የሆለታ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመነጨውን ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት በማስገባት እና ቮልቴጅን በማረጋጋት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የጣቢያው ኃላፊ ገለጹ።
ኃላፊዉ አቶ ጥላሁን አበበ እንደገለፁት በ2008 ዓ.ም. ሥራ የጀመረው ማከፋፈያ ጣቢያው ኃይል በመሸከም እና በቴክኖሎጂ አቅም ከፍተኛነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ነው።
ጣቢያው በሲስተሙ ውስጥ የቮልቴጅ መዋዠቅ እንዳይኖር አውቶማቲክ በሆነ መንገድ ቮልቴጁን የመቆጣጠር እና የመጠበቅ ስራ እንደሚሰራ ኃላፊዉ አብራርተዋል።



ጣቢያው ከህዳሴ በደዴሳ በኩል የሚመጣውን ኃይል ተቀብሎ ወደ 400 ኪሎ ቮልት በመቀነስ ለገላን፣ ለሰበታ እና ለሱልልታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚያደርስ ነው።
ጣቢያው ግሪዱን ከማረጋጋት በተጨማሪ ለአካባቢው ህብረተሰብ እና ለኢንዱስትሪዎች በዘጠኝ ወጪ መስመሮች ለሆለታ ከተማ፣ ለኮሎቦ፣ ለደይሊና አፍሪካ ውሃ አቅርቦት እና ለሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ15፣ በ33 እና በ132 ኪሎ ቮልት መስመሮች የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
በሌላ ዜና የጊንጪ ባለ 230/33/15 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ለአካባቢው ህብረተሰብና ለኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ የጣቢያው ተወካይ ኃላፊ አቶ ዳግም ቱሉ አስታውቀዋል።
ማከፋፈያ ጣቢያዉ በ33 ኪሎ ቮልት ለዳታ ማይኒንግና ብርጭቆ ፋብርካ እንደሁም በ15 ኪሎ ቮልት ለጊንጪ ከተማ፣ ለኬኛ ቢቨሬጅ፣ ጀልዱ፣ ቦዳና ለአኒሞል ፋብሪካ ኃይል እያቀረበ ይገኛል።

የደንዲ ወረዳ አስተዳዳሪ ዶክተር ጉደታ አራርሳ እንደገለጹት ማከፋፈያ ጣቢያ በወረዳው መገንባቱ ቀደም ሲል የነበረውን የኃይል እጥረት በመቅረፍ የአካባቢውን ህብረተሰብ ኑሮ እየቀየረ ይገኛል።
ጣቢያው ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ በወረዳው እና በአካባቢው ከሚገኙ የገጠር ከተሞች መካከል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት መቻላቸውን ገልፀዋል።
በአካባቢው በቂና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በመኖሩ በርካታ ኢንቨስተሮች ወደ ወረዳው መጥተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመሰማራት የልማት ጥያቄዎችን እያቀረቡ እንደሚገኙ አስተዳዳሪው ተናግረዋል።


