ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ ናት የሚለው ትርክት የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም በሚፈለግ መንገድ በዐባይ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የተገነባ ትርክት መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ገለፁ፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ ሞገስ መኮንን “ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ማማ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በዳጉ የቀጥታ ስርጭት ፕሮግራም ላይ በተደረገ ውይይት እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት የሚውል እምቅ የታዳሽ ሀብት አላት፡፡

የተፈጥሮ ሀብቶቿ በሚፈለገው መልኩ በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋሉ ባይሆንም አሁን ላይ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይሏን ከታዳሽ የኃይል ምንጮች ማድረጓና በርካታ ጥቅሞችን እያገኘች መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በየዓመቱ በአማካኝ የ10 በመቶ እድገት እንዳለው የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ከኢንዱስትሪና ከከተሞች መስፋፋት እንዲሁም ከመንግስት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ እያደገ የሚሄደውን የኃይል ፍላጎት ለመሟላት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ተቋሙ “የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል” የመሆን ርዕዩን ለማሳካት በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የታዳሽ ኃይል ልማትን ለማስፋፋት የሚያስችሉ በርካታ መሰረቶችን አስቀምጣ እየሰራች እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሞገስ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ እያበረከተችው ያለው አስተዋጽኦ እና የመሪነት ሚና ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባዔ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር የአፍሪካ ሀገራትን በመሰረተ ልማት ማስተሳሰር የሚለውን የአፍሪካ ሕብረት የነደፈውን አጀንዳ 2063 ለማሳካት ጉልህ ሚና መወጣቷን እና የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ፖሊስ ወደ ተግባር መቀየሩን ከማሳየቱም ባለፈ የውሃ ዲፕሎማሲን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ዕድል እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ናት የሚለው ትርክት ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት በዐባይ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሲቀነቀን የኖረና ሀገሪቱ ያላትን ሀብት በትክክል ከመግለጽ ይልቅ ሀብቶቿን እንዳትጠቀም በሚፈለግ መንገድ የተገነባ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ትርክቱ ኢትዮጵያ የተለያዩ ተፋሰሶች ስላሏት የዐባይ ተፋሰስን እንዳትጠቀም በመፈልግ የተቀነቀነና በተለያዩ ጊዜያት በተፈረሙ የቅኝ ግዛት ውሎች ላይ ቆመው ኢትዮጵያን በዐባይ ተፋሰስ ላይ የልማት ሥራዎች እንዳታከናወን የሚከለክል ትርክት እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ እንደሆነች የሚገለጸውን ትርክት ለመቀየር ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት የሚውሉ ተፋሶችን በአግባቡ መጠቀም እና የተለያዩ የታዳሽ ኃይል ምንጮችን ጥቅም ላይ በማዋል የኃይል ስብጥሩን ማስፋት እንዲሁም ኢትዮጵያን የውሃ ማማ ሳይሆን የታዳሽ ኃይል ማማ መሆኗን ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያን የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማማነት ለማረጋገጥ የትርክት ዳግም ግንባታ ሥራውን ከሀገሪቱ ሀብት፣ ጥቅምና ፍላጎት ጋር በማያያዝ ለኃይል ማመንጫነት በሚውሉ አቅሞች አጠቃቀም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሊንክ፡ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ማማ
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”