የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኬኢሲ ኢንተርናሽናል ከተባለ የህንድ ኩባንያ ጋር የኢትዮጵያ የኃይል ዘርፍ ሪፎርም፣ ኢንቨስትመንት እና ዘመናዊነት (PRIME) ፕሮጀክት ስር የሚከናወኑ የማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታና ማሻሻያ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና በአፍሪካ የኬኢሲ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ሱከሺ ቪያሊ ተፈራርመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጥራት ለማሻሻል፣ የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ እና ተደራሽነትን ለማስፋት ፋይዳው የጎላ ነው።

ስምምነቱ በዓለም ባንክ ድጋፍ ከሚተገበሩ የፕራይም ፕሮጀክቶች መካከል የመጀመሪያው መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በቀጣይ የዲጂታል ስርዓት ዝርጋታን ጨምሮ አዳዲስ የማከፋፈያ ጣቢያዎችና ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች እንደሚተገበሩ ገልጸዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ፕሮጀክቱን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እና ጥራት እንዲጠናቀቅ ኩባንያው በትኩረት እንዲሰራ አሳስበው ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት ተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
በአፍሪካ የኬኢሲ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ሱከሺ ቪያሊ በበኩላቸው ኩባንያው ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን ገልጸዋል።



ስለሆነም ፕሮጀክቱን ከአሁን በፊት የተገኙ ልምዶችን በመጠቀም በጊዜና በጥራት እንደሚያጠናቅቁ አረጋግጠው በፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ከተቋሙ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
170 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታና የማሻሻያ ሥራ ስምምነት የ132 ኪሎ ቮልት ነጠላ ሰርኪዩት ዝርጋታን ለማከናወን የዲዛይን ሥራን ጨምሮ የዕቃ ማምረትና አቅርቦት፣ የዝርጋታ፣ የሙከራና ፍተሻ ሥራዎችን ያጠቃልላል፡፡



