ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል እና በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነቻቸው ያሉ ሥራዎች ዓለም አቀፍ እውቅና እያስገኘላት መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ገለፁ።
ዳይሬክተሩ “ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ማማ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በዳጉ የቀጥታ ስርጭት ፕሮግራም ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የታዳሽ ኃይል ልማትን ለማስፋፋት የሚያስችሉ በርካታ መሰረቶች አስቀምጣ እየሰራች ትገኛለች፡፡
በታዳሽ ኃይል እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ እያከናወነቻቸው ያሉ ሥራዎች ዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ 32) እንድታዘጋጅ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዳስገኘላት አስታውቀዋል፡፡
ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም በተከናወኑ የኮፕ ጉባኤዎች ላይ የአፍሪካ ድምጽ ሆና አቋሟን ስትገልጽ መቆየቷን አቶ ሞገስ አስታውሰዋል።
በታዳሽ የኃይል ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ባከናወነቻቸው ተግባራት የኮፕ 32ን እንድታዘጋጅ መመረጧ፤ ሀገሪቱ በዘርፉ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቷን እና የመሪነት ሚናዋና በአግባቡ እየተወጣች መሆኗን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከራሷ ልማትና ዕድገት ባለፈ አብሮ መልማትና ማደግን እንደ መርህ በመያዝ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በጎረቤት ሀገራት ጭምር ስታካሂድ እንደነበር ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ 95 በመቶ በላይ የሚሆነውን ኃይል ከውሃ እያመነጨች መሆኗን የጠቀሱት አቶ ሞገስ በመላው ሀገሪቱ እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ወደ ግድቦች የሚገባውን ደለል በመቀነስና በመከላከል እንዲሁም የግድቦችን ደህንነት በማስጠበቅ ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ለሀገሪቱ ግድቦች ብቻ ሳይሆን በዐባይ ተፋሰስ ሀገራት የሚገኙ ግድቦችን ደህንነት ጭምር ለማስጠበቅ ስለሚያግዝ የተፋሰሱ ሀገራት ሥራውን ሊደግፉት እና በንቃት ሊሳተፉበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ ልማትና አካባቢያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛየ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ጉባኤ እንድታዘጋጅ መመረጧ ሀገሪቱ በአካባቢ ጥበቃ ላይ እያደረገች ላለው ጥረት እውቅና የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አካባቢን ለመጠበቅ እያከናወነቻቸው ያሉ ሥራዎች ከኢትዮጵያም አልፎ የጎረቤት ሀገራትንና የምስራቅ አፍሪካን የአየር ንበረት ለውጥ ለማስጠበቅ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀው ሀገሪቱ በአካባቢ ጥበቃ ያላትን የመሪነት ሚና ለማስጠበቅ በቀጣይ መሰል ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል፡፡




