የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች ሙስናን ሊጠየፉ ይገባል

የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች ሙስናን ሊጠየፉ ይገባል

ተቋሙ እንደ ሀገር የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት እና ያለውን ሀብት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የተቋሙ ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች ሙስናን ሊጠየፉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሳሰቡ።

“ሥነ-ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥና የጥቅም ግጭትን መከላከል እና ማስተዳደር” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ለተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

በሥልጠናው መክፈቻ ላይ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ  እንደተናገሩትት ተቋሙ በርካታ ሀብት የሚያንቀሳቅስ እና የሥራ ፀባዩ ሙስና በረቀቀ መንገድ ሊፈፀምበት የሚችል በመሆኑ ሁሉም ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።

የሥራ መሪዎች በግዥ ሂደት፣ በፕሮጀክት ትግበራ እና በኦፕሬሽን ሥራዎች ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎችን  በጥንቃቄ መከታተል እና መቆጣጠር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

‘ሙስና ካንሰር ነው’ ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተግባሩ ለረጅም ጊዜ ሳይታወቅ በድብቅና በረቀቀ መንገድ ስለሚፈፀም ተቋምን ብሎም ሀገርን  ለከፍተኛ ኪሳራ ይዳርጋል ብለዋል።

ስለሆነም ተቋሙ እንደ ሀገር የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት እና ያለውን ሀብት ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም የሥራ መሪና ሠራተኛ  ሙስናን በጥብቅ ዲሲፕሊን መታገል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሥልጠናው የሥራ መሪዎች በጥቅም ግጭት  መከላከያ ዘዴዎች ግንዛቤ በመያዝ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ  እንዲወጡ እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

ተቋማዊ የሙስና መከላከል ሥርዐቱን በጥብቅ ዲሲፕሊን በመምራት
ከሙስና የፀዳ ተቋም ለመገንባት የሥራ መሪዎች ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በፌደራል የሥነ- ምግባርና ፀረ -ሙስና   ኮሚሽን የስልጠና መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ የኋላሸት ደሳለኝ በበኩላቸው ተቋሙ ከፍተኛ ሀብት የሚያንቀሳቅስ በመሆኑ ለጥቅም ግጭት ተጋላጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ስልጠናው ለተቋሙ የሥራ መሪዎች በሙስናና መንስኤዎች ለይ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ሥራቸውን ከጥቅም ግጭት በፀዳ መልኩ እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠርና አመራሩ ራሱን እንዲገመግም ለማድረግ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

የሥራ መሪዎች ውሳኔዎችን ሥነ-ምግባርን በተከተለና  ከጥቅም ግጭት በፀዳ መልኩ መስጠት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ስልጠናውን እየሰጡ የሚገኙት በኢትዮጵያ ፐብሊክ  ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የድህረ -ምረቃ ፕሮግራም አስተባባሪ አወቀ አሸናፊ (ዶ/ር)  እንደተናገሩት ስልጠናው ሀገራዊ ተልዕኮውን በአግባቡ ማሳካት የሚችል አመራር ለመፍጠር  ያግዛል።

ለአንድ ቀን በሚሰጠው ስልጠና ላይ የዋና መስሪያ ቤት፣ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ፣ የሪጅንና የፕሮጀክት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

Scroll to Top