ኢትዮጵያ በቀጣናው የጀመረችውን የኃይል ትስስር አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት እያቀረበች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል የበለጠ ለማስፋፋት እየሰራች ነው።
ኢትዮጵያ ለሱዳን፣ ለጅቡቲና ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች መሆኑን ገልጸው ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል እስከ ደቡብ አፍሪካ የማድረስ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።
በቅርቡም ለታንዛኒያ ኃይል ለማቅረብ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመው ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመውሰድ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ንግግር መጀመሯን ገልጸው በቀጣይም በቀጣናው የጀመረችውን የኃይል ትስስር አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው ያረጋገጡት።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ሥርቆት እየተበራከተ መሆኑን ጠቁመው ይህን ለመከላከል የኅብረተሰቡ እና በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት መዋቅሮች ተሳትፎና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል።
የመሰረተ ልማቶች ስርቆት በኤሌክትሪክ የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ተቋማት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እንደሚፈጥር ጠቅሰው ይህም በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ተናግረዋል።