በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሰሜን ሪጅን የሚፈጸመው ተደጋጋሚ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ስርቆት በኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎች ላይ ፈተና እየሆነ መምጣቱን ሪጅኑ አስታወቀ።
በሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመር እና የኦፕቲካል ፋይበር (OPGW) ጥገና ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ ህንፃ ኣረጋዊ እንደገለጹት በሪጅኑ በሁሉም አካባቢዎችበመሰረተ ልማቱ ላይ ስርቆት እየተፈፀመ ቢሆንም በደቡባዊ ምስራቅ ዞን እንደርታ፣ ዋጅራትና አዲጉዶም ወረዳዎች ይበዛል።
ከመቀሌ ማከፋፊያ ጣቢያ ተነስቶ ወደ በርኸሌ ዳሎል በተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ጥምር መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ በተፈጸመ ስርቆት ብቻ 5 ምሰሶዎች መውደቃቸውን አቶ ህንፃ ገልጸዋል።
የተሰረቀውን የታወር ብረት የሚረከባቸው አካል በአቅራቢያቸው ስለሚያገኙ እና በከተሞች ዙሪያ የሚደረገውን ቁጥጥር የላላ በመሆኑ ስርቆቱ በሌሎች አካባቢዎችም ተባብሶ መቀጠሉን ኃላፊው አብራርተዋል።
ይህም ተቋሙን ለአላስፈላጊ ወጪና ለከፍተኛ የሥራ ጫና ከመዳረጉም ባለፈ በአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር አጥፊዎቹን እጅ ከፍንጅ በመያዝ ጭምር ለሕግ እንዲቀርቡ ቢደረግም አስተማሪ እርምጃ ስለማይወሰድ ችግሩ የመባባስ አዝማሚያ ማሳየቱ ጠቁመዋል።
ችግሩን ለመፍታት ለሁሉም ወረዳዎችና ዞኖች በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢያሳውቁም አጥጋቢ መልስ አለማግኘታቸውን የገለጹት አቶ ህንፃ በችግሩ ላይ ለመወያየት ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የታወር ስርቆትን መከላከል ለአንድ አካል ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ሥራ አስኪያጁ የክልሉ የፖለቲካ አመራር፣ የፀጥታና የፍትህ አካላት እና መላው ሕብረተሰቡ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2015 ዓ.ም ብቻ በኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ሥርቆት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ኪሳራ እንዳጋጠመው መዘገባችን ይታወሳል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



