አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ ልማትና ለኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ።
ዋና ስራ አስፈፃሚው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጉባ ባዘጋጀው “ስለ ኢትዮጵያ” መድረክ የፓናል ውይይት ላይ እንደገለፁት ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኃይል መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ያደረገችው ኢንቨስትመንት ለዛሬው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ መሠረት ሆኗል።
ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አሁን ያላትን የኃይል አቅርቦት እስከ አንድ መቶ ሺህ በማድረስ በአስር እጥፍ ማሳደግ እንደሚጠበቅባት ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እየመጡ በመሆኑ ይህን ታሳቢ ያደረገ የኃይል ልማት እንደሚያስፈልግ ዋና ስራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና የኢንደስትሪ ፓርኮች 2 ሺህ 500 ሜጋ ዋት አካባቢ ኃይል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢንዱስትሪ ማዕከል ሆና እንድትወጣና ዓለም አቀፍ ካፒታልን ለመሳብ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት ዋነኛ መወዳደሪያ መሆኑን ዶ/ር ፍሰሃ አስገንዝበዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




