ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሀገር ውስጥ የኃይል አቅርቦት እና ለጎረቤት ሀገራት የኃይል ትስስር ትልቁን ሚና እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለፁ።
“ሕዳሴ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጉባ ባዘጋጀው “የስለ ኢትዮጵያ” መድረክ ላይ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኃይል መሰረተ ልማት አቅም እና ለቀጣናዊ ትስስር በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር እንደገለፁት የኃይል አቅርቦት የሰው ልጅ በምቾት እንዲኖር የሚያደርግ፣ እንደምንተነፍሰው አየር እንደምንመገበው ምግብ ለመኖር ወሳኝ እየሆነ መጥቷል።
በዓለም ላይ ያደጉት ሀገራት የኃይል ማምረት አቅማቸው እና አጠቃቀማቸው ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ኃይል በሌለበት ሀገራዊ እድገት የሚታሰብ አይደለም ብለዋል።
መንግስት በቢሊየን ብሮች መድቦ የኃይል መሰረተ ልማትን እያስፋፋ ያለው ከዚህ መሰረታዊ እሳቤ በመነሳት መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ወደምንፈገልገው ሀገራዊ ብልጽግና ለመድረስና የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የኃይል ማመንጨት አቅማችንን ማሳደግ ወሳኝ ነው።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደጠቀሱት እንደ ሀገር በ80 ዓመት ውስጥ 5 ሺህ ሜጋ ዋት የማይሞላ የነበረውን የማመንጨት አቅም ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ያሳደገው እንዲሁም የምናመርተውን ኢነርጂ በአጭር ጊዜ ከ17 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት ወደ 34 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት ያሳደገው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው።
የህዳሴ ግድብ በበጀት ዓመቱ እስከ ታህሳስ የመጀመሪያ ሳምንት ከመነጨው ኢነርጂ ውስጥ 51 በመቶ ድርሻ ያበረከተ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለሀገር ውስጥ የኃይል አቅርቦት እና ለጎረቤት ሀገራት የኃይል ትስስር ህዳሴ ትልቁን ሚና እየተወጣ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በአግባቡ ከተጠቀምንበት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ አቅም ይፈጥርልናል ብለዋል።
ህዳሴ ከኤክስፓርት ስናገኝ የቆየነውን ከ60 ሚሊየን የማይበልጥ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በማሳደግ ወደ ግማሽ ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ እንድናገኝ አቅም ይሆነናል።
ይህም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የሀገር ውስጥ ተደራሽነት ለማሳደግ እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለማከናወን እድል የሰጠ ነው።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ኃይል ወሳኝ በመሆኑ እንደ ህዳሴ ያሉ ግድቦች ግንባታ ያስፈልጉናል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
