ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለምስራቅ አፍሪካ ትልቅ የታሪክ እጥፋት የፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለምስራቅ አፍሪካ ትልቅ የታሪክ እጥፋት የፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር ትልቅ የታሪክ እጥፋት የፈጠረ፣ ለኢትዮጵያውያን የጋራ አንድነት ማረጋገጫ የሰጠና የታሪካዊ ድሎች ትልቅ ማሳያ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

“ሕዳሴ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ  የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው “የስለ ኢትዮጵያ” መድረክ በጉባ እየተካሄደ ይገኛል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ ግድቡ የሕብረ ብሔራዊ አብሮነት ማጠናከሪያ፣ የብልጽግና አይቀሬነት ማሳያና የኢትዮጵያ የማንሰራራት ምልክት ነው።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከመሠረት ድንጋይ አቀማመጥ ጀምሮ በርካታ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን ማለፉን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነትና በሕዝቡ የተቀናጀ ዲፕሎማሲያዊና የልማት ርብርብ ፕሮጀክቱ እውን መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም ታላላቅ ሥራዎችን መሥራት እንደሚችሉ ለዓለም ያረጋገጡበት “የመሻገር ተምሳሌት” መሆኑንም አክለዋል።

በመድረኩ ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) የህዳሴ ግድብ ለኢንዱስትሪ የሚኖረው ፋይዳ በሚል ርዕሰ ጉዳይ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ የህዳሴ ግድብ እና ንጋት ሀይቅ ለቱሪዝም እድገት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኃይል መሰረተ ልማት አቅም እና ለቀጣናዊ ትስስር እንዲሁም የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ኸይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ለሀገራዊና ቀጣናዊ ትርክት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top