የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለህብረተሰቡ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችላቸውን የትብብርና የመግባቢያ ሥምምነት በዛሬው ዕለት በስካይ ላይት ሆቴል ተፈራርመዋል።
ሥምምነቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት የደንበኞችን እርካታ ለማረጋገጥ፣ የተቋማቱን የፕሮጀክትና የኦፕሬሽን ሥራዎች ውጤታማ ለማድረግ፣ እንዲሁም ወጪና ብክነትን በመቀነስ ገቢን ለማሳደግ ያለመ ነው።
ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለው የአሰራር ሥርዓትና ግንኙነት ተቋማዊ ነጻነትን በጠበቀ መልኩ ከአላስፈላጊ አለመግባባት ይልቅ ትብብርንና መተጋገዝን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት፡፡

የኃይል ልማት ዘርፉ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በጋራ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተቋማቱ በትብብር ስሜትና በኃላፊነት መንፈስ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ሥምምነቱ ከዕቅድ ጀምሮ እስከ አፈጻጸም በጋራ በመስራትና ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው እንደተናገሩት ተቋማቱ ለበርካታ አስርት ዓመታት የዘለቀ የጋራ ጉዞ ቢኖራቸውም ባለፉት 12 ዓመታት ግን በኃይል መሰረተ ልማት ዘርፍ በአዋጅ ተለያይተው የተሰጣቸውን ተልዕኮና ራዕይ ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

ሥምምነቱ በተቋማቱ መካከል አዲስ የአሰራር ሥርዓትና ባህል ለመገንባት የሚኖረው አስተዋፅዖ የጎላ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።
እንደ ኢንጂነር ጌቱ ገለፃ ሁለቱ ተቋማት የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት ለማሻሻልና ለደንበኞች የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል።
የተቋማቱ አመራሮች ሥምምነቱን እስከ ታች በማውረድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና ውጤት ለማስመዝገብ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።







