የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሰው ሀብት ልማት፣ በምርምርና በማማከር ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ተፈራርመዋል፡፡
ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ -ሥርዓቱ ወቅት እንደገለፁት ተቋሙ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ በኃይል ልማት ዘርፉ የሠለጠነ ብቁ ባለሙያ ያስፈልገዋል፡፡
ስምምነቱ ተቋሙ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር ያለውን የቆየ ግንኙነት በማጠናከር የተቋሙ ሠራተኞች በዩኒቨርሲቲው በኃይል ኢኮኖሚክስ እና በኃይል ምህንድስና የትምህርት መስኮች የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ይህም ዘርፉ የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ተቋሙ የያዘውን የረጅም እና የአጭር ጊዜ ዕቅድ ለማሳካት ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ስምምነቱ በዘርፉ ላይ በሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች እና በማማከር ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት እንደሚያስችል የጠቆሙት ኢኒጂነር አሸብር በኃይል ልማት ዘርፍ የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመገንባት ተቋሙ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ዩኒቨርስቲው የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ራስ ገዝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለሀገራዊ ፍላጎቶች ቀዳሚ ምላሽ የሚሰጥና ችግር ፈች የምርምር ሥራዎች የሚከናወኑበት እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዳበረ ኢኮኖሚ ለመገንባት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ከመሰሉ ተቋማት ጋር በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማማከር ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ የመግባቢያ ሥምምነቶች እየተፈረሙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ሳሙኤል ገለፃ ከተቋሙ ጋር የተደረገው ሥምምነት ሀገሪቱ በኃይል ልማት ዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም የኃይል ተደራሽነቱን ለማስፋት እና የአፍሪካ ሀገራትን በኃይል ለማስተሳሰር የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው የራሱን ድርሻ እንዲወጣ የሚያስችለው ነው።
ስምምነቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እና መምህራን በተቋሙ የሥራ ላይ የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበትን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አብራርተዋል፡፡
ትብብሩ የተሳካ ይሆን ዘንድ ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”






