ሪጅኑ በአራት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ቅየራ ሥራ አከናውኗል

ሪጅኑ በአራት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ቅየራ ሥራ አከናውኗል

በእርጅና ምክንያት በኦፕሬሽን ሥራ ላይ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ የአራት ማከፋፈያ ጣቢያ መቆጣጠሪያ ወይም ብሬከሮችን በአዲስ ጂ አይ ኤስ ዘመናዊ መቆጣጠሪያዎች የመቀየር ሥራ ማከናወኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማዕከላዊ ሦስት ሪጅን አስታወቀ፡፡

የሪጅኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ እስማኤል ሙዘይን እንዳስታወቁት በሪጅኑ 1 ሺ 108 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የማስተላለፊያ መስመሮች እና ከባለ 132 እስከ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የቮልቴጅ መጠን ያላቸው 20 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡

በሪጅኑ ብዛት ያላቸው ማከፋፈያ ጣቢያዎች ረጅም ጊዜ ያገለገሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ብሬከሮች በእርጅና ምክንያት በኦፕሬሽን ሥራዎች እና በኃይል አቅርቦቱ ላይ እንቅፋት ሲፈጥሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ሪጅኑ ችግሩን በመቅረፍ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ በ2017 በጀት ዓመት የአሰላ፣ የአዳሚ ቱሉ፣ የወልቂጤ እና የሰበታ ሁለትን ማከፋፈያ ጣቢያዎች መቆጣጠሪያዎችን በዘመናዊ ጂ አይ ኤስ የመቆጣጠሪያ መቀየሩን ገልፀዋል፡፡

በሌሎች አራት ማከፋፈያ ጣቢያዎችም ተመሳሳይ ሥራ ለማከናወን ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡

አቶ እስማኤል እንደገለፁት በአዲስ ዌስት እና ወልቂጤ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የትራንስፎርመር ቅየራ እንዲሁም በቃሊቲ አንድ – ወረገኑ እና በሰበታ አንድ – መካኒሳ የ132 ኪሎ ቮልት ከረንት ትራንስፎርመር አቅም የማሳደግ ሥራ ተከናውኗል፡፡

ከአቅም ማሳደግና ማዘመን ሥራው ጎን ለጎን ሪጅኑ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ መደበኛ የኢንስፔክሽን እና ጥገና ሥራዎችን በማከናወን እንዲሁም የውስጥ አሰራርን በማዘመን ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሪጅኑ የሚከናወኑ የአቅም ማሳደግ እና የማዘመን ሥራዎች የኃይል ብክነትን በመቀነስ፣ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን በማቀላጠፍ እና የኃይል መቋረጥ ጊዜን በማሳጠር የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለማሳደግ እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ሪጅኑ የሠራተኞችን አቅም ለማሳደግ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለ421 ሠራተኞች ሥልጠና መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top