ተቋሙ የያዘውን ርዕይ ለማሳካት የባለሙያውን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ

ተቋሙ የያዘውን ርዕይ ለማሳካት የባለሙያውን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ

በኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ በሚከናወኑ የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና የሲቪል ግንባታ ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ሠራተኞችን አቅም ለማሳደግ  ለአንድ ወር ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ።

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰው ሀብት ሥራ አስፈፃሚ አቶ አታላይ አበበ  እንደተናገሩት የተቋሙ የራስ ኃይል በሀገር ውስጥና በውጭ ለማከናወን የያዘውን ርዕይ ለማሳካት የባለሙያውን አቅም በማሳደግ የሰርተፊኬት ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ይጠይቃል።

ተቋሙ በትምህርት ያልተደገፉ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን የሰርተፊኬት ባለቤት ለማድረግ የስልጠና ስርዓት ቀርፆ  ስልጠናዎችን በራስ አቅም መስጠት መጀመሩን ተናግረው በቀጣይ መሠል ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ከመረጃ አያያዝ ጀምሮ የፕሮጀክቶቹን አፈፃፀም ለማሻሻል ሠራተኞች ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

በተቋሙ የኢትዮ ፓወር አካዳሚ ዳይሬክተር ወንድወሰን ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ስልጠናው የራስ ኃይልን አሁን ካለበት ደረጃ ለማሳደግ ከፋተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

አካዳሚው በሠራተኞች ላይ የሚስተዋሉ የክህሎትና የዕውቀት ክፍተቶችን በመለየት በራስ አቅም ስልጠናዎችን ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ከተቋሙ ተልዕኮ ጋር በተያያዘ ብቃት ያለው ባለሙያ ለማፍራት እስከ ደረጃ 5 ባለሙያዎችን ለማሰልጠን አቅዶ እየሰራ  መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ የምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተወካይ አቶ ግርማ ዘለቀ እንደተናገሩት ስልጠናው ሠራተኞች በልምድ ያገኙትን እውቀት ከንድፈ ሃሳብ ጋር በማቀናጀት ሥራቸውን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዲያከናውኑ ለማድረግ፣ ሥራውን ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ለማከናወን፣ ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን እና  አለመግባባቶችን ለመቅረፍ ያግዛል።

በዘርፉ የሀብት አስተዳደር መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ መንበረ ክፍሌ በበኩላቸው ሠራተኞች እየሰሩበት ያለው የሥራ ፀባይ ራሳቸውን በትምህርት እንዳያሳድጉና የሚፈልጉት ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ ማድረጉን አንስተዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ የኢትዮ ፓወር አካዳሚ ስልጠናውን በማመቻቸቱ አመስግነው ሠልጣኖች ስልጠናው መነሻ እንጅ መዳረሻ አለመሆኑን ተገንዝበው በቀጣይ ራሳቸውን በተለያዩ መንገዶች ማብቃት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በራስ አቅም በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ እየሰሩ የሚገኙ ሠራተኞችን አቅም ለማሳደግ የተሠጠው ስልጠና ከዚህ በፊት በሠራተኞች ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን አንዱ ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ የተቋሙ መሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር ጸሐፊ አቶ ሀይሉ ወልዴ ናቸው፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከስልጠናው ዘመኑን የዋጀ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዕለቱም ለአንደ ወር በቆየው ስልጠና ላይ የተሳተፉ 41 የሲቪል እና 12 የኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታ ባለሙያዎች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top