በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ እና የውሳኔ ሰጪነት ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሴቶች የኢነርጂ ባለሙያዎች ማህበር (EWiEN) ለአምስተኛ ጊዜ በኢነርጂ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ዓመታዊ መርሃግብር በሒልተን ሆቴል እያካሔደ ይገኛል።
በመርሃግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተወካይ ወንድወሰን ካሳ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ተቋሙ ሴቶች በኢነርጂ ዘርፉ ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።



ተቋሙ የኢትዮጵያ ሴቶች የኢነርጂ ባለሙያዎች ማህበር ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል።
እንደ ወንድወሰን(ዶ/ር) ገለፃ መርሃግብሩ ሴቶች በዘርፉ ላገኙት ስኬት ዕውቅና ከመስጠት ጎን ለጎን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የአቅም ማሳደግ ሥራዎችን ለመስራት ያግዛል።
ማህበሩ በዘርፉ የሴት ባለሙያዎችን ዕድገት እና ተሳትፎ ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያደንቁ ገልፀው ተቋሙ በሁሉም ደረጃዎች የሴት ባለሙያዎችን ቁጥር ለመጨመር በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በመርሃግብሩ ላይ በኢነርጂ ዘርፍ ላይ የተሳተፉ ተቋማትና ድርጅቶች ምርታቸውንና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት አውደርዕይ የተከፈተ ሲሆን በዘርፉ የሴቶች ተሳትፎ ዕድገት ላይ ትኩረቱን ያደረገ የፓናል ውይይትም እየተካሔደ ይገኛል።


ማህበሩ በዓመቱ በኢነርጂ ዘርፍ ላይ በፈጠራና በአስተዳደር እንዲሁም በልዩ ልዩ ደረጃዎች ተፅዕኖ ለፈጠሩ ሴቶች ዕውቅና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ሴቶች የኢነርጂ ባለሙያዎች ማህበር (EWiEN) በኢነርጂ ዘርፍ ያለውን የሥርዓተ-ፆታ ክፍተት ለማመጣጠን በማሰብ በአምስት ሴት ባለሙያዎች የተመሠረተ ለትርፍ ያልተቋቋመና መንግሥታዊ ያልሆነ ማህበር ነው፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”