ተቋሙ የኃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል

ተቋሙ የኃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2018 በጀት ዓመት የመንግስት የልማት እና ኢነርጂ ፖሊሲዎችን ታሳቢ ያደረገ የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለፁት ተቋሙ ባለፉት ስድስት ዓመታት ብቻ በኃይል ማመንጨት ዘርፉ ላይ ያከናወናቸው ሥራዎች በ128 ዓመታት ከተከናወኑ ሥራዎች የ48 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡

ተቋሙ ባለፉት ስድስት ዓመታት ባከናወናቸው የግንባታ ሥራዎች ሀገራዊ የማመንጨት አቅሙን በ3 ሺህ 784 ሜጋ ዋት ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት የፕሮጀክት አስተዳደር አቅምን በማሳደግ ተቋሙ ግንባታቸው የተጀመሩ የማመንጫ፣ የማስተላለፊያ መስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችን በመከታተል እና በመቆጣጠር እንዲሁም የተጠናቀቁትን ወደ ኦፕሬሽን ለማስገባት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እና የአሰላ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ያሉት ኢንጂነር አሸብር የአይሻ፣ የኮይሻ እና የአሉቶ ጅኦተርማል ፕሪይም ፕሮጀክቶችን በመከታተልና በመቆጣጠር አፈፃፀማቸውን ለማሻሻል ዕቅድ ተይዞ ለተግባራዊነቱ እንቅስቃሴ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ፣ የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን፣ የባህር ዳር-ወልድያ- ኮምቦልቻ እና የአዋሽ-ወልዲያ የባቡር ኃይል አቅርቦት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ አስር የማስተላለፊያ መስመሮችን እና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ግንባታ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት እንደሚሰራ ነው ያነሱት፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ የኢትዮ-ጂቡቲ 2ኛ ሰርኪዩት እና የጎንደር-ዳንሻ-ሁመራ-ባዕከር አግሮ ኢንዱስትሪ የኃይል አቅርቦት እንዲሁም የመቀሌ-ዳሎል የኃይል ማስተላለፊያ መስመርን ጨምሮ የሰባት ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማስጀመር ዕቅድ ተይዟል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የኃይል አማራጮች 38 ሺህ 120 ጊጋ ዋት ሰዓት ለማምረት መታቀዱንና ከዚህም ውስጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የ45 ነጥብ 21 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ደንበኞች 31 ሺህ 600 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል  በማቅረብ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች በአጠቃላይ 109 ነጥብ 54 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ለ2018 በጀት ዓመት ለሥራ ማስኬጃ 251 ቢሊየን ብር በጀት የያዘ ሲሆን 55 ነጥብ 1 ከመቶ ከኃይል ሽያጭና ልዩ ልዩ ገቢዎች፣ 31 ነጥብ 4 ከመቶ ከሀገር ውስጥ ብድርና እርዳታ እንዲሁም 13 ነጥብ 5 ከመቶ ከዓለም አቀፍ  ብድርና እርዳታ እንደሚሸፈን ተገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከተያዘው 251 ቢሊየን ብር ውስጥ 71 በመቶ ለፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ እንደሚውል የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው 118 ቢሊዮን ብር በግንባታ ሂደት ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች፣ 29 ቢሊዮን ብር ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች ማስጀመሪያ እና 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለመልሶ ግንባታ ሥራ እንዲሁም ቀሪው 17 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብሩ ለመለዋወጫ ዕቃዎች ግዥ እና ለሲቪል ጥገና ክፍያዎች መመደቡን አብራርተዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top