የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተሽከርካሪና የነዳጅ አስተዳደርን ለማዘመንና ብክነትን ለመቀነስ የዘረጋቸው አዳዲስ አሠራሮች ውጤት እያመጡ መሆኑን በተቋሙ የተሽከርካሪ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ እንደገለፁት ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በ27 ዋና ዋና መስመሮች ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 26ቱ በራሱ ተሽርካሪዎች የሚሸፈኑ ናቸው፡፡

ከእነዚህ መስመሮች መካከል 16ቱ ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም በተቋሙ የትራንስፖርትና የነዳጅ አጠቃቀም ሥርዓት ላይ አዲስ ምዕራፍ ከመክፈቱም ባሻገር በዓመት ለነዳጅ ይወጣ የነበረውን ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ለማዳን አስችሏል ብለዋል፡፡
በተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብዛት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በአሰላ እና በሐዋሳ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በነዳጅ የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ ለመተካት 55 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ግዢ የጨረታ ግምገማ ተጠናቋል፡፡
በሌላ በኩል ቢሮው በቴክኖሎጂ የታገዘ የተሽከርካሪዎች ቁጥጥር በመጀመሩ አላስፈላጊ የሀብት ብክነትን ከመቀነስ ባለፈ ለተሸከርካሪዎች ደህንነት ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
የተሸከርካሪዎችን የጂ.ፒ.ኤስ መረጃዎችን ከነዳጅ አጠቃቀም ጋር በማቀናጀት የተሟላ የስምሪትና የነዳጅ ቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት ጎ ላይቭ (Go Live) የተሰኘ አዲስ የሞተር ፑል ሶፍትዌር ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት፡፡