የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኢትዮ- ጅቡቲ ሁለተኛ ሰርኪዩት የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለመገንባትና ለማሻሻል የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ከኤም ቢ ኤች ፓዎር ኩባንያ የገበያና ቢዝነስ ልማት ኃላፊ ቪካሽ ኩማር ጋር ተፈራርመዋል፡፡
ኢንጂነር አሸብር በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ወቅት እንደገለፁት ተቋሙ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን የኃይል ትስስር በማጠናከር በምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት (EAPP) ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ ከጂቡቲ ጋር ያለውን የኃይል ትስስር ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል።
ሥራ ተቋራጩ የፕሮጀክቱን ሚና በመገንዘብ በተያዘለት ጊዜ፣ በጀትና ስምምነቱ ላይ በተቀመጡ መስፈርቶች መሠረት ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንዲሰራ ኢንጂነር አሸብር አሳስበዋል።
ኩባንያው ከፕሮጀክቶቹ የግንባታ ሥራ ጎን ለጎን ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር እንዲያደርግም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠይቀዋል።
በኤም ቢ ኤች ፓወር የገበያና ቢስነስ ልማት ኃላፊ ቪካሽ ኩማር በበኩላቸው ኩባንያቸው የኢትዮ- ጂቡቲ ሁለተኛ ሰርኪዩት አካል የሆኑትን የሚሌ ባለ 230 ኪሎ ቮልት አዲስ ማከፉፈያ ጣቢያ ግንባታ እንዲሁም በኮምቦልቻ 2 እና ሰመራ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የማስፋፊያ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

ኩባንያው ከዚህ በፊት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ያገኘውን ልምድ ተጠቅሞ ፕሮጀክቱን መንግስትና ተቋሙ በሚፈልገው መልኩ አጠናቆ ለማስረከብ በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ተወካይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ደስታለም ኃይሉ እንደገለፁት የተደረገው ስምምነት አንድ የአዲስ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታና የሁለት ማከፋፈያ ጣቢያዎች የማስፋፊያ ሥራዎችን ያካትታል።

ፕሮጀክቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኃይል አቅርቦት ለማሳደግና በሚሌና አካባቢው ተጨማሪ ኃይል ለመስጠት እንደሚያግዝም አንስተዋል ።
ለማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ግንባታና ማስፋፊያ በአፍሪካ ልማት ባንክ 25 ሚሊየን ዶላርና በተቋሙ የሚሸፈን 14 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተመድቧል፡፡ ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በሁርሶ በኩል ወደ ጅቡቲ ከሚሄደው መስመር በተጨማሪ በሚሌ በኩል ለጅቡቲ በአማራጭ ኃይል ለመስጠት የሚያስችል ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡



