የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምስራቃዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ማስፋፊያ አካል የሆነውን የድሬዳዋ- ጅግጅጋ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ከኬ ኢ ሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘ የህንድ ኩባንያ የአፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ሱኬሽ ቫውሊ ጋር ተፈራርመዋል፡፡

ኢንጂነር አሸብር በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ወቅት እንደገለፁት ተቋሙ በሀገር ውስጥ ያለውን የግሪድ ሥርዓት በማጠናከር አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ የምስራቁን የኤሌክትሪክ ኔትወርክ ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል።
ሥራ ተቋራጩ የፕሮጀክቱን ሚና በመገንዘብ በተያዘለት ጊዜ፣ በጀትና ስምምነቱ ላይ በተቀመጡ መስፈርቶች መሠረት ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንዲሰራም ኢንጂነር አሸብር አሳስበዋል።
በኬኢሲ ኢንተርናሽናል ኩባንያ የአፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ሱኬሽ ቫውሊ ኩባንያቸው የምስራቃዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክትን በስምምነቱ ላይ በተቀመጡ መስፈርቶች መሠረት፣ በተያዘለት ጊዜና በጀት አጠናቆ ለማስረከብ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ተወካይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ደስታለም ኃይሉ እንደገለፁት የምስራቃዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የድሬዳዋ- ጅግጅጋ ባለ 400 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ 160 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡
ፕሮጀክቱ የምስራቁን ግሪድ ከማጠናከር ባለፈ ለፋፈን የመስኖ ፕሮጀክትና ለምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ እንዲሁም በቀጣይ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል በኩል ለሚደረገው የውጭ የኃይል ትስስር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል።
እንደ ኢንጂነር ደስታለም ገለፃ ለማስተላለፊያ መስመሩ ግንባታ በአፍሪካ ልማት ባንክ እና ኮሪያ ኤግዚም ባንክ የሚሸፈን የ48 ነጥብ 42 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እና በተቋሙ የሚሸፈን 28 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦለታል።



