የመሰረተ ልማት ጥበቃ በሚጠናከርበት ዙሪያ ውይይት ተካሔደ

የመሰረተ ልማት ጥበቃ በሚጠናከርበት ዙሪያ ውይይት ተካሔደ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች ከለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ጥበቃ በሚጠናከርበት ዙሪያ ውይይት አካሄዱ።

በውይይቱ ላይ በክፍለ ከተማው ወረዳ 3፣ 4 እና 6 ውስጥ በሚገኙ የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ተደጋጋሚ ስርቆት እንደሚፈፀምና ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት ጥበቃ ክፍተት እንዳለባቸው ተነስቷል።

የማዕከላዊ ሪጅን 1 ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ገዛኸኝ በክፍለ ከተማው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ የብረት ማማዎች ስርቆትና ህገ-ወጥ ግንባታዎች መስፋፋታቸውን በመግለጽ ክፍለ ከተማውን አቋርጦ በሚሄደው የ230 ኪሎ ቮልት የለገጣፎ-ቃሊቲ 1 ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ የሚፈጸመው ስርቆት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አብራርተዋል።

ከአንድ ወር በፊት በዚሁ ክፍለ ከተማ በስርቆት እና እሱን ተከትሎ በነበረው ከባድ ንፋስ ምክንያት 5 የብረት ማማዎች በመውደቃቸው ከብሔራዊ የኃይል ቋት ከ50 እስከ 65 ሜጋ ዋት የሚደርስ ኃይል መቀነሱን በአጽንኦት ተናግረዋል።

በተጨማሪም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈፀሙ የስርቆትና ተዛማጅ ወንጀሎች የወደቁ የብረት ማማዎችን መልሶ ለመገንባትና ወደ አገልግሎት ለመመለስ ተቋሙ ከ40 ሚሊዮን ብር  በላይ ኪሳራ የደረሰበት መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ክፍለ ከተማውን አቋርጠው በሚያልፉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ተደጋጋሚ የስርቆት ወንጀል በመፈፀሙ በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡንና እሱን ተከትሎ በኃይል ተጠቃሚዎች ላይ ቅሬታ መፈጠሩን የገለፁት ደግሞ የማዕከላዊ ሪጅን 2 ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ዘበርጋ ናቸው።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከክፍለ ከተማና ከወረዳ አመራሮች ጋር የተቀናጀ ትብብር ለመፍጠር ውይይት መካሄዱን የገለፁት አቶ አለማየሁ መፍትሔ ያሏቸውን ሃሳቦች በውውይቱ ላይ አቅርበዋል።

እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ወሳኝ የሀገር ሀብት መሆናቸውን በውል በመረዳት፣ በወንጀል ፈጻሚዎች ላይ አስተማሪ የሆነ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል።

በህብረተሰቡ ዘንድ የግንዛቤና የጥበቃ ሰንሰለት በመፍጠርና አጥፊዎችን ወደ ህግ በማቅረብ የክስ ሂደቱን መከታተልና ከኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ የብረት ማማዎች ስር የሚካሄዱ ህገ-ወጥ ግንባታዎችን ማስቆም እንደሚገባም ነው የገለፁት።

የክፍለ ከተማው የሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ  አቶ አየለ ለሚ በበኩላቸው የመሰረተ ልማት ጥበቃ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ወይም የፖሊስ ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ማህበረሰብን ጨምሮ የአመራሮች እና የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን በመገንዘብ ችግሩን ለመፍታት ሁሉንም ባሳተፈና በተቀናጀ መንገድ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የማዕከላዊ ሪጅን 1 እና 2 የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማና የወረዳ አስተዳደር  አመራሮች፣ የፖሊስ፣ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች እንዲሁም የመሬት አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

Scroll to Top