ተቋሙ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በማበረታታት የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ እየሰራ ነው

ተቋሙ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በማበረታታት የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ እየሰራ ነው


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለዘርፉ የሚያስፈልጉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማበረታታት የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡

የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያዘጋጀውን የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመገኘት ጉብኝተዋል፡፡

በተቋሙ የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኽኝ እንደገለጹት የጉብኝቱ ዓላማ የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች በሀገሪቱ እየተከናወኑ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ልማት እንቅስቃሴዎችን በመረዳት ተቋሙ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ ለማድረግ ነው፡፡

በኤግዚቢሺኑ ላይ ምርታቸውን ያቀረቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች ህልውናቸው የተመሰረተው በአስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ላይ በመሆኑ ተቋሙ ለኢንዱስትሪው ዕድገት አስፈላጊውን የኃይል አቅርቦትና ድጋፍ በማድረግ ረገድ ያለውን ከፍተኛ ሚናም ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተቋሙ የኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ውድነህ የማነ በበኩላቸው የሀገር ውስጥ ምርቶች በየዓመቱ በጥራትና በብዛት እያደጉ ለመምጣታቸው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝ መሆን ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር ውድነህ ገለጻ ሀገሪቱ ቀደም ሲል ስታመርታቸው ከነበሩ ምርቶች በተጨማሪ ማዕድን ማቀነባበርን ጨምሮ ወደ ከባድ ኢንዱስትሪዎች የተሸጋገሩ ተቋማት መበራከታቸው እጅግ ከፍተኛ ኃይል የሚጠይቅ በመሆኑ ተቋሙ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት በሰፊው እየሰራ ይገኛል።

በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የኢንዱስትሪ ዕድገት ተከትሎ የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎችን ለመመለስ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ቀደም ሲል እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት የግንባታ ግብዐቶች ከውጭ የሚገቡ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በከፍተኛ ቮልቴጅ ደረጃ ኬብሎችን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመሩ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረትና በራስ አቅም ለመመራት የሚያስችል ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከባለሀብቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለዘርፉ የሚያስፈልጉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች በሃገር ውስጥ እንዲመረቱ በማበረታታት የውጭ ምንዛሬና ጥገኝነትን ለመቀነስ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡

በጉብኝቱ የተሳተፉ ሠራተኞች በ”ኢትዮጵያ ታምርት” የቀረቡ ምርቶች የኢነርጂና የኢንዱስትሪ ዘርፎች የማይነጣጠሉ መሆናቸውን የተገነዘቡበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top