በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምስራቅ አንድ ሪጅን በ2018 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የኃይል አቅርቦትን አስተማማኝነት ለማሻሻል በርካታ ተግባራዊ ሥራዎች አከናውኗል።
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ወርዲ ሙሐመድ እንደገለጹት፣ በዚህ ወቅት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ማዘመን፣ የሠራተኞችን አቅም ማሳደግ እና መደበኛና ድንገተኛ የጥገና እና ፍተሻ ሥራዎችን በተስፋፋ መልኩ ማከናወን ተችሏል።
ባለፉት 9 ወራት ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል፦



✅ የመስመር ፍተሻ እና ጥገና፦ በተለያዩ የኪሎ ቮልት መጠን ባላቸው 3 ሺህ 822 ነጥብ 47 ኪሎ ሜትር የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የፍተሻ እና የጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል።
✅ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ማዘመን፦ በአደጋ ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመከላከል በሐረር እና በድሬደዋ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የብሬከር ቅየራ ሥራዎች ተጠናቀዋል።
✅ የአደጋ ጊዜ መፍትሔ፦ በአዲጋላ ማከፋፈያ ጣቢያ ብሬከር ላይ ያጋጠመውን ችግር ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ በመትከል በአጭር ጊዜ የተቀረፈ ሲሆን፣ ነባሩን ጣቢያ በዘላቂነት ለመጠገን ርብርብ እየተደረገ ነው።
✅ አቅምን ማሳደግ፦ በድሬዳዋ ቁጥር 3 ጣቢያ ላይ 125 ሜጋ ቮልት አምፒየር አቅም ያለው ትራንስፎርመር ለመቀየር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀዋል።
✅ የንፋስ ኃይል አጠቃቀም፦ የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ተመርቆ ወደ ሥራ በመግባቱ ሪጅኑ ተጨማሪ እና ንጹሕ ኃይል እንዲያገኝ ተደርጓል።
✅ የመልሶ ግንባታ ሥራ፦ ከአሰበ ተፈሪ – አፍደም በተዘረጋው መስመር ላይ በስርቆት ምክንያት ወድቆ የነበረው የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶ (Tower) በሪጅኑ አቅም ተገንብቶ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል።
ተቋሙ የኦፕሬሽን እና የጥገና ሥራዎችን ለማዘመን የሚተገብራቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ውጤታማ ለማድረግ ለሠራተኞች ተከታታይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በምስራቅ አንድ ሪጅን ሥር ያሉ 8 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች (አዲጋላ፣ ሁርሶ፣ ድሬደዋ 1፣ 2 እና 3፣ ሐረር፣ አሰበ ተፈሪ እና አዋሽ 7 ኪሎ) አስተማማኝ ኃይል እንዲያቀርቡ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል!


