በዓለም ባንክ ፋይናንስ ተደርገው በሚሰሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕራይም-1 ፕሮጀክቶች ላይ የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖ ስጋቶችን መቆጣጠር እንደሚገባ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የአካባቢ እና ማህበራዊ ስጋት አስተዳደር ቡድን ጋር በመተባበር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ከደቡብ ሱዳን ለተውጣጡ ባለሙያዎች በአካባቢ እና ማህበራዊ ስጋት አስተዳደር ዙሪያ በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡


በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ከፍተኛ ማህበራዊ ልማት ስፔሻሊስት ሚስተር ፓረታፐሪያ ጎሽ እንደገለጹት በፕሮጀክቶች ላይ ከማህበራዊና አካባቢያዊ ስጋት አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት በፕሮጀክቶች ውስጥ የሚያጋጥሙ የአካባቢ እና ማህበራዊ ስጋቶችን በመቆጣጠር ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟሉ እንዲሆኑ ሥልጠናው ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ የሚከናወኑ የፕራይም-1 ፕሮጀክቶችን በመወከል የተገኙት አቶ እውነቱ ጌትነት እንደተናገሩት በዓለም ባንክ ፋይናንስ ተደርገው 15 የኃይል ማከፋፈያ እና ማስተላለፊያ መስመሮች እንደሚገነቡ ገልፀዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹም የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖን በመቀነስ መልኩ በባንኩ የአካባቢ እና ማህበራዊ ጥበቃ መስፈርት መሠረት ግንባታቸውን ለማከናወን ለፕራይም ፕሮጀክቶች የተቀጠሩ የአካባቢ፣ የማህበራዊ እና ጤና እና ደህንነት ባለሙያዎች የአቅም ማሳደግ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደተቋም የሚከናወኑ ሥራዎች ማህበረሰብ አቀፍ በመሆናቸው ሥልጠናው በፕሮጀክቶች ትግበራ ላይ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ይረዳል የሚል እምነት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡
በተቋሙ የአካባቢና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሪት ሜሮን ዮሐንስ በበኩላቸው የዓለም ባንክ ፋይናንስ በሚያደርገው ፕራይም -1 ኮምፖነት- 2 ስር ከሚገኙ 15 ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ፕሮጀክቶች ውስጥ ለ10 ፕሮጀክቶች የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲሁም ለ 4 ፐሮጀክቶች የመልሶ ማስፈር መርሃ ግብር ጥናቶች ተጠናቀው በአበዳሪወ ይሁንታን በማግኘት በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በኩል መጽደቻቸውን አብራርተዋል፡፡

ቢሮው አሁን ላይ የ2 ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቶችን የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖዎችን ግምገማ እና የመልሶ ማቋቋም ጥናቶችን እየተከታተለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም በኮፖነንት 3 ሥር ለሚገኙ የጂኦተርማል ፕሮጀክቶች ጥናቶችን ለማስጠናት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና በዓለም ባንክ መካከል ባለው የአካባቢያዊና ማህበራዊ የቁርጠኝነት ዕቅድ መሰረት 11 የአካባቢያዊ፣ የማህበራዊ እና የጤና ባለሙያዎች መቀጠራቸውን ያስታወሱት ወ/ሪት ሜሮን ሠራተኞቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት አቅማቸውን ለማጎልበት ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡፡
ሥልጠናው በተቋሙ የተሰሩ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ ሰነዶች ተግባራዊ በሚደረጉበት መንገድ እና በሥራ ላይ በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ዙሪያ ትኩረት አድርጎ ለቀጣዮች 5 ቀናት የሚሰጥ ይሆናል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

