
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት 29 ሺ 480 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማምረቱን አስታወቀ።
ተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን በስካይ ላይት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጠ ነው።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ 25 ሺ 423 ጊጋ ዋት ሰዓት ለማምረት ታቅዶ 29 ሺ 480 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማምረት ተችሏል።
ይህም ከዓመታዊ ዕቅዱ የ16 በመቶ ወይም 4 ሺ 56 ጊጋ ዋት ሰዓት እንዲሁም በ2016 በጀት ዓመት ከተመረተው 20 ሺ 596 ጊጋ ዋት ሰዓት የ43 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ በበጀት ዓመቱ ከመነጨው ውስጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 9 ሺ 798 ጊጋ ዋት ስዓት ወይም የ33 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም የጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ 7 ሺ 148 ጊጋ ዋት ሰዓት ወይም የ24 ነጥብ 2 በመቶ በማመንጨት ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው።
በበጀት ዓመቱ ከመነጨው ኃይል 28 ሺ 682 ጊጋ ዋት ሰዓቱ ወይም 97 ነጥብ 3 በመቶ ከውኃ እንዲሁም 789 ጊጋ ዋት ሰዓቱ ወይም 2 ነጥብ 7 በመቶ ከንፋስ የተገኘ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ እና የአሰላ ንፋስ የተወሰኑ ተርባይኖች ወደ ኦፕሬሽን መግባት፣ የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ጠንካራና ቀጣይነት ያላቸው የጥገና ሥራዎች መከናወን፣ የመለዋወጫ ዕቃ አቅርቦቱ መሻሻል ለዕቅድ አፈጻጸሙ ከፍ ማለት በምክንያትነት አንስተዋል።
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ያስመዘገበውን ስኬት እንደመነሻ በመጠቀም በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዓለም አቀፍ እውቅና ካላቸው የሲስተም ኦፕሬተሮች ጋር በጥገናና ኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ አብሮ በመስራት፣ የማመንጫ ጣቢያዎችን አቅም በማሻሻልና በማዘመን እንዲሁም የክትትልና ድጋፍ ሥርዓቱን በማጠናከር እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ህዳሴን እና አሰላ ኃይል ማመንጫዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ኦፕሬሽን በማስገባት በ2018 በጀት ዓመት 38 ሺ 124 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማምረት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



