ተቋሙ ማኅበረሰቡን እያገለገለ ትርፋማ መሆን ችሏል

ተቋሙ ማኅበረሰቡን እያገለገለ ትርፋማ መሆን ችሏል


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ማኅበረሰቡን እያገለገለ ትርፋማ መሆን ይቻላል የሚለውን አመለካከት በመያዙ ትርፋማ መሆን መቻሉን የተቋሙ የፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ፡፡

ሥራ አስፈፃሚው አቶ አለማየሁ መንግስቱ እንደገለፁት መንግስት ያከናወናቸው የለውጥ ሥራዎች፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና አተቋሙ ሥራ አመራር ቦርድ የሰጣቸው አቅጣጫዎች እና የተቋሙ ማኔጅመንት የወሰዳቸው ርምጃዎች የፋይናንስ ጤናማነቱን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው፡፡

ተቋሙ ከስድስት ዓመት በፊት የበጀቱን 89 ያህል በመቶ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በሚያገኘው ብድር ይሸፍን እንደነበረ እና የእዳና ሀብት ምጣኔው 99 ለ 1 ደርሶ እንደነበር ሥራ አስፈፃሚው አስታውሰዋል፡፡

ይሁንና ሀገራዊ ለውጡ ከተቋሙ ዕዳና ሀብት አስተዳደር፣ ከፕሮጀክቶች አፈጻጸም እና ከኦፕሬሽን ሥራዎች መሻሻል ጋር ጉልህ ለውጥ በማምጣቱ በ2018 በጀት ዓመት የተቋሙ የሀብት መጠን 9 መቶ ቢሊየን ብር መሻገሩንና የተቋሙን በጀት ከ75 በመቶ በላይ ወጪ በራሱ መሸፈን መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

ተቋሙ የገቢ አማራጮችን ማስፋቱ፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸው፣ የኃይል ሽያጩን ከብር በተጨማሪ በዶላር ማከናወኑ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ዕዳው መሰረዙ ለተመዘገበው ተቋማዊ ለውጥ የድርሻቸውን አበርክተዋል ብለዋል፡፡

ተቋሙ እንደ አዲስ ሲቋቋም ከነበረው የ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ዓመታዊ ገቢ ተነስቶ በ2016 በጀት ዓመት 27 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን፣ በ2017 በጀት ዓመት ገቢው ወደ 72 ቢሊየን ብር ማደጉንና በ2018 በጀት ዓመት 124 ቢሊየን ብር ገቢ ተገኝቶ ተቋሙ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ማትረፉን ለአብነት አንስተዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ተቋሙ ሀገራዊ ለውጡ ከፈጠራቸው ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር እንዲተዳደር መደረጉ ማኅበረሰቡን እያገለገለ ትርፋማ መሆን ይቻላል የሚለውን አመለካከት በመያዝ ለውጥ ማምጣትና ትርፋማ መሆን ችሏል፡፡

Scroll to Top