በሪጅኑ የትራንስፎርመሮችን ደህንነት ለማስጠበቅ ጥብቅ አሰራር ተዘርግቷል

በሪጅኑ የትራንስፎርመሮችን ደህንነት ለማስጠበቅ ጥብቅ አሰራር ተዘርግቷል

በማዕከላዊ ሪጅን 1 በሚገኙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚገኙ ትራንስፎርመሮችን ደህንነት ለማስጠበቅ ጥብቅ  የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን የሪጅኑ ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡

ዳይሬክተሩ አቶ ደረጀ ገዛኸኝ እንደገለፁት በትራንስፎርመሮች ላይ በሚያጋጥሙ የቴክኒክ ብልሽቶች እና ባልተጠበቁ አደጋዎች ምክንያት የሚከሰቱ የኃይል መቋረጦችን ለመከላከል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

የትራንስፎርመሮችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከየማከፋፊያ ጣቢያዎቹ የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ የደህንነትና ቁጥጥር ቡድን የተዋቀረ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ሥራዎችን በቅንጅት ለማከናወን እንዳስቻለ ተናግረዋል፡፡

የትራንስፎርመሮችን የውስጥና የውጭ የሙቀት ሁኔታ፣ የዘይት መጠንና ንፅህና መከታተል የቡድኑ ዋነኛ ተግባር መሆኑንም ነው አቶ ደረጀ ያብራሩት፡፡

ዘይቱ የትራንስፎርመሩን የውስጥ አካላት ከማቀዝቀዙ ባሻገር የማለስለስ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ የዘይት ናሙናዎች እየተወሰዱ መደበኛ የላቦራቶሪ ምርመራ እንደሚደረግላቸው ገልፀዋል።

ባለሙያዎቹ ትራንስፎርመሮቹ ከመጠን በላይ ኃይል እንዳይጫኑ በመከታተል እና የቮልቴጅ መዛባት እንዳይገጥማቸው በማድረግ የክትትል ሥራዎች እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም በወጪ መስመሮች ላይ ኃይል በተደጋጋሚ ሲቋረጥ በትራንስፎርመሮች  ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ የአደጋ ቅድመ ማሳወቂያ መሳሪያዎች መገጠማቸውን ተናግረዋል፡፡

በዘመናዊ የኢኢፒ ማስተር ድረገጽን መሰረት ያደረገ መተግበሪያ ታግዞ የትራንስፎርመሮችን መረጃ በየሰዓቱ መመዝገብ መቻሉን ጠቅሰው ይህም ፈጣን የጥገና ውሳኔ ለመስጠትና የትራንስፎርመሮችን የአገልግሎት ዘመን ለማራዘም አስችሏል ብለዋል።

የእነዚህ ቴክኖሎጂዎች መተግበር ተቋሙን ከአላስፈላጊ ወጪዎች ማዳኑን ነው ያብራሩት፡፡

Scroll to Top