በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕፃናት ማቆያ ማዕከል የቆይታ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ 24 ሕፃናት ወደ ቅድመ-መደበኛ ትምህርት በመሸጋገራቸው በዛሬው ዕለት የሽኝት ፕሮግራም ተደርጎላቸዋል።
በሽኝት መርሃ-ግብሩ ላይ የተቋሙ የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ተወካይ ኃላፊ ግርማ ግዛቸው (ዶ/ር) እንደተናገሩት የማዕከሉ መቋቋም ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ ሙሉ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ አስችሏል፡፡

ሕፃናቱ የመጀመሪያ ደረጃ ማህበራዊ እና አዕምሯዊ ዕድገታቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲያዳብሩ ማዕከሉ ትልቅ አስተዋፅዖ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
የሕፃናት ማቆያው መቋቋም ሴት ሠራተኞች ከማንኛውም ሥጋትና ጭንቀት ነፃ ሆነው በሥራ ቦታቸው ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ ማቻሉን ነው የጠቆሙት፡፡
ይህም ተቋሙ የሥራ ምርታማነቱ እንዲጨምርና የሴት ሠራተኞች ተነሳሽነት ከፍ እንዲል አዎንታዊ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል፡፡
በተቋሙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ እንደገለፁት 24 ሕፃናት በማቆያ ማዕከሉ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ቅድመ-መደበኛ ትምህርት ተሸጋግረዋል።

በቀጣይም በአዋሽ 2ኛ እና 3ኛ እንዲሁም በአዳማ 1ኛ እና 2ኛ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የቆይታ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ 7 ሕፃናት ተመሳሳይ የሽኝት መርሃ-ግብር እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
የሕፃናት ማቆያ ማዕከሉ የተቋሙን ሴት ሠራተኞች የሥራ ጫና ከማቃለል ባሻገር የኢትዮጵያን የነገ ብሩህ ጉዞ የሚወስኑ ሕፃናትን የተሟላ ስብዕና ከመቅረጽ አኳያ ትልቅ መሠረት እየጣለ መሆኑ ጠቅሰዋል፡፡


እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ታዳጊ ሕፃናቱ በማዕከሉ የቆይታ ጊዜያቸው ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ ፍቅርን፣ አብሮነትንና ማህበራዊ መስተጋብርን በማጎልበት ራሳቸውን በተሻለ መልኩ የሚገልፁበት ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡
በሽኝት መርሃ-ግብሩ ወቅት ሕፃናቱ በማዕከሉ የነበራቸውን ቆይታ የሚያስታውሱ የተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎችንም አቅርበዋል፡፡
የሕፃናት ማቆያ ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት ከአራት ወር እስከ አራት ዓመት የሚደርሱ 82 የተቋሙ ሠራተኞች ልጆችን ተቀብሎ በመንከባከብ ላይ ይገኛል።





