ተቋማቱ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ዘመናዊ አውቶብሶችን ለስፖርት ክለቡ አስረከቡ

ተቋማቱ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ዘመናዊ አውቶብሶችን ለስፖርት ክለቡ አስረከቡ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለኢትዮ- ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ አገልግሎት የሚሰጡ በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የተገጣጠሙ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸውን ሁለት ዘመናዊ አውቶብሶችን ገዝተው አስረከቡ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት ሁለቱ ተቋማት ከኃይል ዘርፉ ባሻገር የኢትዮ- ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብን በማቋቋም በስፖርት ዘርፍ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል፡፡

የስፖርት ክለቡ የሁለቱ ተቋማት አንድነት መገለጫ በመሆን በእግር ኳስ፣ በሩጫ እና በቴኒስ ዘርፎች በሁለቱም ጾታዎች በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ስፖርተኞችን በማቀፍ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የአውቶብስ ርክክቡ የስፖርት ክለቡ ከአሁን ቀደም ለተሸከርካሪ ኪራይ ያወጣ የነበረውን ወጭ ከማስቀረቱ ባለፈ የስፖርተኞችን እንግልት በማስወገድ ለክለቡ ውጤታማነት የጎላ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመሆን የስፖርት ክለቡን ውጤታማነት የሚያረጋግጡና የስፖርተኞችን እንግልት የሚያስወግዱ መሰል ድጋፎች ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሳፕላይ ቼይን፣ የንብረትና ጠቅላላ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ለምለም ምስጋናው የስፖርት ክለቡ ከሁለቱ ተቋማት ባሻገር ሀገርንና አህጉርን ያስጠሩ ስመጥር ስፖርተኞችን በማፍራት በኩል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአውቶብስ ርክክቡ ተቋማቱ ለስፖርት ክለቡ የሰጡትን ትኩረት ማሳያ መሆኑን ያነሱት ሥራ አስፈጻሚዋ የስፖርት ክለቡ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትጋት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ መንግስቴ በበኩላቸው የስፖርት ክለቡ ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራቸውን ወክለው በመወዳደር የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ያደረጉ ዕውቅ ስፖርተኞችን እያፈራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የስፖርት ክለቡ ለረጅም ዘመናት በውጤታማነት የመቀጠሉ ምክንያት የተቋማቱ ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ክለቡ በቀጣይ በሚኖረው ኦሎምፒክ ላይ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት የቦርድ ሰብሳቢው መሰል ድጋፎች የስፖርተኞችን ሞራል በመገንባት በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ ለስፖርት ክለቡ ለሚያደርጉት ያልተቋረጠ ድጋፍ ለሁለቱ ተቋማት አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የአውቶሞቲቭ አማካሪ አቶ ኃይሉ ዘርጋው ኩባንያው ኩባንያው የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በመገጣጠም በስፋት ለገበያ በማቅረብ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የተያዘውን ሀገራዊ ዕቅድ እየደገፈ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡

ኩባንያው ከተቋማቱ ጋር በመተባበር የስፖርት ክለቡን ውጤታማነት የሚያሳድግ የአውሮፓ ደረጃዎችን ያሟላ ዘመናዊ አውቶብስ ገጣጥሞ በማስረከቡ ታላቅ ደስታ እንደሚሰማው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በጥገና፣ በመለዋወጫ ዕቃ አቅርቦት እና በሌሎች ጉዳዮች ከተቋማቱ ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

Scroll to Top