የዘርፎች አሰራር ከተቋም ዕቅድና ስትራቴጂ ጋር የተናበበ መሆኑን የሚገመግም የመስክ ምልከታ ተካሄደ

የዘርፎች አሰራር ከተቋም ዕቅድና ስትራቴጂ ጋር የተናበበ መሆኑን የሚገመግም የመስክ ምልከታ ተካሄደ

የዘርፎች አሰራር ከተቋም ዕቅድና ስትራቴጂ ጋር የተናበበ እና ተቋማዊ ለውጥ የሚያመጣ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በተቋሙ የኮርፖሬት ገቨርናንስና ኮምፕሊያንስ ዘርፍ ሥር የሚገኙ የሥራ ክፍሎች በፓወር ግሪድ ኦፕሬሽን እና በወረገኑ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

በዚህ ወቅት የዘርፉ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዱጉማ ነዳ እንደገለፁት የመስክ ምልከታው በተቋሙ ውስጥ የሚገኙ ዘርፎች ከኦፕሬሽንና አስተዳደራዊ ሥራዎች ጋር በተያያዘ እያጋጠሟቸው ያሉ ችግሮችን፣ የአመራር ድጋፍ የሚፈልጉ ጉዳዮችን እና ከተቋም ዕቅድና ስትራቴጂ አንፃር እየተመሩበት ያለውን አግባብ ለመገምገም ያለመ ነው፡፡

በምልከታው የተለዩ ችግሮችን በዕቅድ ውስጥ በማካተት እና ከሚመለከታቸው የሥራ ዘርፎች በጋራ በመሆን ለመፍታት ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ቀጣይነት ያለው ለውጥ እንዲያስመዘግብ ምልከታው ፕሮጀክቶችን ባካተተ መልኩ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡

ዘርፉ የተነሱ ችግሮች በየደረጃው የሚፈቱበትን አግባብ ከማመቻቸትና ድጋፍ ከመስጠት ጀምሮ መፍትሔ ማግኘታቸውን በመከታተል ግብረ መልስ እንደሚሰጥ ሥራ አስፈፃሚው አስገንዝበዋል፡፡

በተቋሙ የፓወር ግሪድ ኦፕሬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሚኪያስ ወንድሙ የግሪድ ኦፕሬሽን ሥራዎች የተቋሙ አጠቃላይ ቁመና የሚታይበት ቦታ በመሆኑ የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶ መሰራት ያለባቸው ተግባራት መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

የመስክ ምልከታው መምሪያው እያከናወናቸው በሚገኙ ሥራዎች እና በሚያጋጥሙት ችግሮች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ የግሪዱን አስተማማኝነት ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዘርፉ የድርሻውን እንዲወጣ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማንሳት ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲቀርቡ መቆየታቸውን የተናገሩት አቶ ሚኪያስ ከዘርፉና ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ጋር በትብብር በመስራት ለችግሮቹ ዘላቂ እልባት ለመስጠት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይም ሌሎች የዘርፍ ኃላፊዎች መሰል የመስክ ምልከታ በማድረግ ግሪዱ ያለበትን ሁኔታ በማየትና በመጎብኘት መታገዝ ያለበትን እንዲያግዙ፣ የሚፈቱ ችግሮችንም እንዲፈቱ በማድረግ ለተሻለ ውጤት በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

የወረገኑ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሸዋ በበኩላቸው ጣቢያው ለፓወር ግሪድ ኦፕሬሽን እና አካባቢው አስተማማኝ ኤሌክትሪክ እያቀረበ እንደሆነና ካለው የኃይል ፍላጎት አንጻር ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራዎችን ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በኮርፖሬት ገቨርናንስና ኮምፕሊያንስ ዘርፍ የተደረገው የመስክ ምልከታ ጣቢያው እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችንና እያጋጠሙት የሚገኙ ተግዳሮቶች ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የመስክ ምልከታው የሠራተኛውን ተነሳሽነትና የእኔነት ስሜት እንደሚያሳድግ የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ የተነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረትም ጣቢያው ከዘርፉ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top