በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ለመመለስ በቅንጅት እየተሰራ ነው

በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ለመመለስ በቅንጅት እየተሰራ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በቢሾፍቱ ከተማና አካባቢው ያለውን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገለፀ፡፡

በተቋሙ የቢሾፍቱ ቁጥር ሦስት ባለ 400 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ አይቼው እንደገለፁት ቢሾፍቱ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦትን የሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎችና የቱሪስት መዳረሻዎች ያሉባት ከተማ ናት።

ማከፋፈያ ጣቢያው ከገላን ማከፋፈያ ጣቢያ በባለ 400 ኪሎ ቮልት በጥምር መስመር ኃይል ተቀብሎ 400/230 ኪሎ ቮልት የሚቀይሩ 1200 ሜጋ ቮልት አምፔር ወይም 960 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ያላቸው ሁለት አውቶ ትራንስፎርመሮች አሉት ብለዋል።

ጣቢያው በ230 ኪሎ ቮልት በጥምር መስመር ለዱከም፣ ለቢሾፍቱ እና ለሞጆ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል እያቀረበ ሲሆን ጣቢያው ካለው ከ960 ሜጋ ዋት የመጫን አቅም ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው 140 ሜጋ ዋት ብቻ መሆኑንም ገልፀዋል።

ጣቢያው አገልግሎት መስጠት በጀመረበት ወቅት ለቢሾፍቱ ከተማና ኢንዱስትሪዎች ታስበው የተተከሉት 100 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ሁለት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ፓወር ትራንስፎርመሮች ብቻ እንደነበሩት የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ በአካባቢው በ 33 ኪሎ ቮልት የኃይል ጥያቄ በመኖሩ 100 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ሁለት ተጨማሪ ፓወር ትራንስፎርመሮች መተከላቸውን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት አስር ባለ 15 ኪሎ ቮልት እንዲሁም አስራ ሁለት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች እንዳሉትና ከእነዚህም ውስጥ ዘጠኝ ባለ 15 ኪሎ ቮልት እና ስምንት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ለከተማውና ለኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ቀሪዎቹ መስመሮች ደግሞ ለዳታ ማይኒግ ድርጅት ኃይል እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የጣቢያው ባለ 33 ኪሎ ቮልት ፖወር ትራንስፎርመር በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሲሳይ ከፋብሪካዎችና ከኢንዱስትሪዎች የሚቀርበውን ተጨማሪ የኃይል ጥያቄ ተቀብሎ ለማስተናገድ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

በቢሾፍቱ ከተማና አካባቢው ከፍተኛ የኃይል አቅርቦትን የሚጠይቁ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ፍሰት እየጨመረ በመምጣቱ የኃይል ፍላጎቱ የጣቢያው ግንባታና የአቅም ማሳደግ ሥራዎች ሲከናወኑ ይመጣል ተብሎ ከታሰበው በላይ በፍጥነት እያደገ መምጣቱን አብራርተዋል።

ስለሆነም እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት በአግባቡ ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቢሾፍቱ ቁጥር ሁለት ደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ዳምጠው በበኩላቸው የኃይል ብክነትን በቀነሰ መልኩ ለደንበኞች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ በቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኙት ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ያለ በመሆኑ ይሄን ታሳቢ በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ አስታውሰዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top