ቀጣናዊ የኃይል ትስስር ለመፍጠር አዳዲስ የፋይናንስ ምንጮችን መፈተሸ እንደሚገባ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዎን ጤሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
አፍሪ-ራን በተሰኘው እና ምክንያታዊ የናይል ወንዝ አጠቃቀም እና ቀጣናዊ ውህደት በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ምክክሩ በአካባቢው ትብብርን ለማጠናከር ጥሩ እርምጃ መሆኑን አንስተዋል።
ለዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት፣ ለሥራ ፈጠራ እና ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም አስተማማኝ እና ፍትሃዊ የኃይል አቅርቦት መሰረት ሆኖ ማገልገል አለበት ያሉት ሚኒስትሩ ይህንን ለማሳካት የጋራ መሰረተ ልማት፣ የተጣጣሙ ፖሊሲዎች እና ድንበር ተሻጋሪ የኃይል ንግድ የአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳን እቅዶች ለማሳካት ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በአፍሪካ ሚሊየኖች የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኙ በመሆናቸው ቤቶች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ኢኮኖሚን ለማነቃቃት እና ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማሰማራት የጋራ ፍላጎትን ማሰባሰብ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋትና ቀጣናዊ የኃይል ትስስር ለማጠናከር አዳዲስ የፋይናንስ ምንጮች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።
አፍሪራን ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ የናይል ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ገዢ መርህ በማድረግ በናይል ወንዝ ፍትሐዊነት ማረጋገጥ እንዲቻል ዓላማ ይዞ የተቋቋመ ዓመታዊ ቀጣናዊ ኮንፈረንስ ሲሆን ዘንድሮ በዋናነት ትኩረቱን የመንግሰትና የግል ሴክተር ትብብር የፋይናንስ ምንጮች ላይ አድርጎ መክሯል።
“ቀጣናዊ የኃይል ትስስር ለአካታችና ዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
