የሞጆ ቁጥር ሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ በአረርቲ አካባቢ የነበረውን የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሽ በመቀነስ አስተማማኝ ኃይል እያቀረበ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ሚናስ ወንድምሞላ እንደገለጹት ጣቢያው በ2013 ዓ.ም 80 ሜጋ ዋት ኃይል የመጫን አቅም ባላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች ነው ሥራ የጀመረው።
ጣቢያው በ15 ኪሎ ቮልት ስድስት ወጭ መስመሮች ሲኖሩት ለሞጆ ከተማ፣ ለኢፌዲሪ አየር ኃይል፣ ለሞጆ ቆዳ ፋብሪካ፣ ለአዳማ ውሃ እና ለደረቅ ወደብ ኃይል እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ለአረርቲ ከተማ ኃይል ከጣቢያው ለማቅረብ በተቋሙ የራስ ኃይል አማካኝነት የማስፋፊያ ሥራ በማከናወን 25 ሜጋ ቮልት አምፔር የመጫን አቅም ያለው ባለ 33 ሺ ኪሎ ቮልት ትራንስፎርመር መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
ትራንስፎርመሩ ከአረርቲ በተጨማሪ ለኤጀሬ ከተማ፣ ለአንበሳ ቢራ ፋብሪካ እና ለአረርቲ ሴራሚክ ኃይል የሚሰጡ አራት ወጪ መስመሮች እንደተዘጋጁ ገልጸዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ለረጅም ጊዜ የመቆራረጥ ችግር የነበረበት ወደ አረርቲ የሚሄደው መስመር ዋንኛ ችግር ለአረርቲ፣ ለኤጀሬና ለአረርቲ ሴራሚክስ በአንድ ሰርኪዩት ብሬከር ኃይል ይሰጥ ስለነበረ ነው።
በዚህ ምክንያት በወር ውስጥ እስከ 234 ጊዜ የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሽ ይመዘገብ እንደነበረ የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ይህም ለደንበኞች ቅሬታ እና ብሬከሩን ለብልሽት ዳርጎ ነበር ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ሦስቱም መስመሮች በተናጠል በተዘጋጀው ብሬከር አገልግሎት በመስጠቱ የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሹ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡
ይህም በተደጋጋሚ በሚከሰቱ የኃይል መቋረጦች ምክንያት ብሬከሩ ላይ ያጋጥም የነበረውም የመሳሪያ ብልሽት ከማስቀረቱም ባሻገር ያልተቆራረጠ ኃይል ማቅረብ ማስቻሉን ገልፀዋል፡፡
ለአረርቲና አካባቢው ተብሎ የተተከለው ትራንስፎርመር 20 ሜጋ ዋት የመጫን አቅም ያለው ቢሆንም እስከአሁን ጥቅም ላይ የዋለው ግን ከዘጠኝ ሜጋ ዋት ያልበለጠውን ነው ብለዋል።
በአካባቢው ከዋናው መስመር ተለይተው ወደ ውስጥ የሚገቡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ንዑስ ጣቢያዎች በመኖራቸው ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት ንዑስ ጣቢያዎችን ሄዶ ለመክፈት የሚወስደው ጊዜ ኃይል የመቋረጥ ስዓቱን ያረዝመዋል ነው ያሉት፡፡
ከአገልግሎት መስጫ ማዕከሉ ጋር በመነጋገር የተሻለ መስመር የማፅዳት ሥራ እንዲከናወን ለማድረግ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ሚናስ ከአካባቢው ተጨማሪ የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ቢመጣ ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው የነበረው የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሹ በከፍተኛ ደረጃ ቢቀንስም ሙሉ በሙሉ ችግሩን ለመቅረፍ ከሞጆ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ጣቢያው ካለው 100 ሜጋ ዋት የመጫን አቅም ውስጥ በአሁኑ ወቅት ጥቅም ላይ የዋለው 25 ሜጋ ዋት አካባቢ ነው ያሉት አቶ ሚናስ የዳታ ማይኒንግ ድርጅት ወደ ሥራ እየገባ በመሆኑ ተጨማሪ ኃይል ጥቅም ላይ ይውላል በሚል እምነት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



