የጣና ነሽ 2 ጀልባ ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
በተቋሙ የምስራቅ አንድ ሪጅን የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይ ዘወልዴ እንደገለፁት በተሸከርካሪ ተጭነው በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ስር የሚያቋርጡ ከፍታ ያላቸው ብረት ነክ ዕቃዎች ዓለም አቀፍ አሰራሮችን በጠበቀ መልኩ እንዲያልፉ እየተደረገ ነው፡፡
በጣና ሀይቅ ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠትና የቱሪዝም ፍሰቱን ለማሳደግ ታስቦ ከጅቡቲ ዶራሌህ ወደብ ወደ ባህር ዳር እየተጓጓዘች የምትገኘው ጣና ነሽ 2 ጀልባ አዳማ ከተማ እስከምትደርስ ድረስ የኃይል መስመሮች ጉዳት እንዳያደርሱ የመጠበቅ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
ጀልባዋ ጉዞ ማድረግ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ አዳማ ከተማ እስከምትደርስ ድረስ ባለ 230 እና 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የሚያልፉባቸው 53 ቦታዎችን ችግር ሳያጋጥም በተሳካ ሁኔታ ማቋረጧን ገልፀዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮቹን ለአጭር ሰዓት ኤሌክትሪክ በማቋረጥ ለጀልባዋ ጉዞ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ተችሏል፡፡
የማዕከላዊ 2 ሪጅን የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና ባለሙያ አቶ ሙሉቀን ወልደማሪያም በበኩላቸው ከአዋሽ ሰባት ኪሎ እስከ ቆቃ በተዘረጋው መስመር ላይ የጀልባዋን ጉዞ ለማሳለጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ተቋሙ ጀልባዋ ጉዞ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው በቀጣይም በምታልፍባቸው ቦታዎችም ተመሳሳይ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል፡፡
የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ከመሬት ያላቸውን ከፍታ በዘመናዊ መሳሪያ በመለካት መረጃዎችን ማደራጀት መቻሉም ተገልጿል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



