የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዘርፉ የሰለጠነና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ከኃይል ማመንጫና ማስተላለፊያ የሥራ ዘርፎች ጋር በተያያዙ አራት የሙያ መስኮች ላይ ላለፈው አንድ ወር ሲያከናውን የቆየውን የሙያ ደረጃና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት አጠናቋል።
በዝግጅት ሥራው ከተቋሙ፣ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከጀኔራል ዊንጌት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲሁም ከነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የተውጣጡ 35 ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ሥራዎቹ በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ፣ በማከፋፈያ ጣቢያ ኤሌክትሮሜካኒካል ግንባታ እንዲሁም በኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ኦፕሬሽንና ጥገና የሙያ መስኮች ላይ ያተኩሩ ናቸው።
የሙያ ደረጃዎቹና የሥርዓተ ትምህርቶቹ የተዘጋጁት ዓለም አቀፍና ሀገራዊ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና አሰራር ማዕቀፎችን፣ የኃይል ዘርፉን ልዩ ባህሪያትና የተቋሙን የሥራ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ነው።
ይህም በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት በሙያ መስኮቹ ከደረጃ 2 እስከ 5 የሚሰጡ ሥልጠናዎች ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የጠበቁ፣ ከዘመናዊ መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች ጋር የተጣጣሙ እንዲሁም የተቋሙን የሰው ኃይል ፍላጎት የሚያሟሉ እንዲሆኑ ያስችላል።
በተጨማሪም ተቋማቱ ወጥነት ያለው ሥርዓተ ትምህርት በመተግበር ለኃይል ልማት ዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን እንዲያፈሩ ከማገዝ ባለፈ የተቋሙ ፓወር አካዳሚ በዘርፉ ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችለውን ዕውቅና እንዲያገኝ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
በቀጣይ ለአራቱም የሙያ መስኮች የሥልጠና ማኑዋሎች፣ የማስተማሪያና የመማሪያ መርጃ ቁሳቁሶች እንዲሁም የምዘና ሥርዓቶች የሚዘጋጁ ሲሆን ሰነዶቹ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጸደቁ በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንደሚደረጉም ተገልጿል።
#የኢትዮጵያ_ኤሌክትሪክ_ኃይል