በ2019 በጀት ዓመት ቀሪ ወራት ሁሉም የተቋሙ አመራሮች በመደመር እሳቤና በጊዜ የለኝም መንፈስ በመሥራት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አሳሰቡ።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተቋሙ የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምን ከአመራሮቹ ጋር ባደረገው የግምገማ ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት ተቋሙ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በሩብ ዓመቱ ሥራዎችን ተቀናጅቶ ከማከናወን፣ ከፕሮጀክት አፈፃፃም፣ ከሀብት አስተዳደር እንዲሁም ከተቋማዊ ገፅታና የሥራ ባህል ግንባታ ጋር ተያይዞ ክፍተቶች መታየታቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም አመራሩ ሠራተኛውን በማስተባበር እነዚህንና ሌሎች ክፍተቶችን በሚያርም እንዲሁም ያልተሠሩ ሥራዎችን በሚያካክስ መልኩ በጊዜ የለኝም መንፈስ መሥራት እንዳለበት ገልፀዋል።
ከኮፕ-32 ጋር ተያይዞ በተቋሙ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ሁሉም በቅንጅት እንዲሰራም ነው ኢንጂነር አሸብር ያሳሰቡት።
በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የኦፕሬሽንና የግዥ ሥራዎችን በማዘመን፣ የፕሮጀክት አፈፃፀምን በማሻሻል፣ ወጪን በመቀነስ፣ የገቢ አሰባሰብንና ዲጂታላይዜሽንን በማሳደግ እንዲሁም ሀብትን በአግባቡ በማስተዳደር መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ጊዜው የመፍጠንና የመፍጠር በመሆኑ የተቋሙን አሠራሮች በማዘመን ለላቀ ውጤትና ለሀገራዊ ብልጽግና በትብብርና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
#የኢትዮጵያ_ኤሌክትሪክ_ኃይል