በኮምቦልቻ አንድ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፊያ ጣቢያ ካሉት ሁለት ትራንስፎርመሮች መካከል በአንደኛው ላይ ባጋጠመ ችግር ምክንያት በከፊል ተቋርጦ የቆየው ኃይል ዳግም መመለሱን የሰሜን ምስራቅ 1 ሪጅን አስታወቀ።
በሪጅኑ የኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ በድሩ አህመድ እንደገለፁት 40 ሜጋ ቮልት አምፒር ኃይል የመጫን አቅም ባለው ትራንስፎርመር ላይ ባጋጠመ የእሳት አደጋ ምክንያት ለአንድ ወር ያህል በአካባቢው በከፊል ኤሌክትሪክ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡


በዚህም በትራንስፎርመሩ ታፕ ቼንጀር ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች እና በአካባቢያቸው በከፊል የኃይል ተቋርጦ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ጉዳት የደረሰበትን ባለ 132/66/15 ኪሎ ቮልት ትራንስፎርመር ጠግኖ ዳግም አገልግሎት ለማስጀመር ከሪጅኑ እና ከማዕከል የተውጣጡ የጥገና ባለሙያዎች ርብርብ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ነው የገለፁት።
በአካባቢው በከፊል ተቋርጦ የቆየውን የኤሌክትሪክ ኃይል በዛሬው ዕለት ሙሉ በሙሉ መመለስ ተችሏል ያሉት አቶ በድሩ በጥገና ሥራው ላይ ርብርብ ሲያደርጉ ለነበሩ የጥገና ባለሙያዎች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

