በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚገኙ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) መሰረተ ልማቶች ለሳይበር ጥቃት እንዳይጋለጡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በተቋሙ የሳይበር ደህንነት መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ጌትነት አድማሱ እንዳስታወቁት የኢንተርኔት እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም አጠቃቀም ማደጉን ተከትሎ የሳይበር ደህንነት ስጋት ተጋላጭነት በዓለም አቀፍ ብሎም በሀገር ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

የሳይበር ደህንነት መምሪያ ዳይሬክተር
ይህን ተከትሎም በተቋሙ የሚከናወኑ የአሰራር ሥርዓቶች በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲከናወኑ የሚያግዙ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ላይ የሳይበር ጥቃት እንዳያጋጥም ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጀምሮ መተግበሪያዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ ሰርቨሮች እንዲሁም የኔትዎርክ ዕቃዎችን የሳይበር ደህንነት ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የዲጂታላይዜሽን አሰራሮች ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ በሶፍትዌሮች እና ሀርድዌሮች ግዥ ላይ የሳይበር ደህንነት መስፈርቶች እንዲሟሉ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ የአሰራር ሥርዓቶች መዘርጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሳፕ ኢአርፒን (SAP ERP) የመሳሰሉ አሰራር ማዘመኛዎችን ጨምሮ በተቋሙና በውጭ እየለሙ የሚገኙ ሶፍትዌሮች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የሳይበር ደህንነት መመዘኛዎችን ማሟላታቸውንና ለጥቃት ተጋላጭ መሆንና አለመሆናቸውን ፍተሻና ክትትል እንደሚደረግባቸው ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ወደ ሥራ ከገቡ በኋላም በእያንዳንዱ ሲስተም ላይ የተለያዩ የሳይበር ደህንነት መከታተያ የአስራር ሥርዓቶችን በመተግበር እና ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ደህንነታቸውን የማስጠበቅና የመቆጣጠር ሥራ እየተከናወነ ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም በተቋሙ ኔትወርክ ላይ ማንኛውም ሰው ከተቋሙ ዕውቅና ውጭ ኢንተርኔትም ሆነ የተቋሙን ሲስተም መጠቀም እንዳይቻል የሚያደርጉ የደህንነት ማስጠበቂያ አሰራሮች መዘርጋታቸውን አቶ ጌትነት አስረድተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ በእያንዳንዱ ሲስተም ላይ ያሉ የጥቃት አጋላጭ ዓይነነቶችን አስቀድሞ በመለየት የመከላከል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የመረጃ መንታፊዎች ቴክኖሎጂዎችን ሰብሮ ከመግባት ይልቅ በሰው አማካኝነት በቀላሉ የሳይበር ጥቃት የማድረስ አቅም እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ጌትነት ይህን በመገንዘብም በተቋሙ በሳይበር ደህንነት ምህዳር ላይ ንቃተ ሕሊና ያለው ሠራተኛ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡
የተቋሙን የሳይበር ደህንነት ለማረጋገጥ ክፍሉ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የተቋሙ የሥራ መሪ እና ሠራተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ተገንዝቦ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”