የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2017 በጀት ዓመት በዶላር ከሚከናወን የኃይል ሽያጭ 263 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን በተቋሙ የፋይናንስ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ፡፡
ሥራ አስፈፃሚው አቶ ደመረ አሰፋ እንዳስታወቁት ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ለጎረቤት ሀገራት እና በዳታ ማይኒንግ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ከሚያቀርበው የኃይል ሽያጭ 263 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዷል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የታቀደው በ2016 በጀት ዓመት የተገኘውን ገቢ በእጥፍ አካባቢ ከፍ ያለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ በሀገሪቱ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ የተቋሙን ገቢ ከፍ እንደሚያደርገው ጠቁመው ይህም የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኃይል እየቀረበላቸው ካሉ የውጭ ሀገራት በተጨማሪ በተያዘው በጀት ዓመት ለታንዛኒያ ኃይል ለማቅረብ ዕቅድ መያዙ ሀገሪቱ ለምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ዕድገት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል፡፡
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”