በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የተከናወኑት የፍተሻና ጥገና ስራዎች ያልተቆራረጠ፣ ጥራት ያለውና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ማድረጋቸውን በዘርፉ የዕቅድ አፈፃፀም ክትትልና ትንተና ቢሮ አሰታወቀ፡፡
የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ ታገል ደገፋ እንዳስታወቁት ዘርፉ የ2016 በጀት ዓመት የኃይል አቅርቦቱ አስተማማኝ እንዲሆን ለማድረግ ተደራሽነቱን ለማስፋፋት በ31 ሺህ 669 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው የማስተላለፊያ መስመር ላይ ፍተሻ በማከናወን 25 ሺህ 338 ነጥብ 36 ኪሎ ሜትር መስመር ተጠግኗል፡፡
ከዚህም በተጓዳኝ በማከፋፈያ ጣቢያዎች በ9 ሺህ 281 ቤዮች ላይ የፍተሻ ሥራ በማከናወን 8 ሺህ 5 ነጥብ 88 ቤዮችን መጠገናቸውን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
ስማርት ሜትር ባልተተከለባቸው የማከፋፈያ ጣቢያዎች የስማርት ሜትር ተከላ መገጠሙንና የ15 እና 33 ኪሎ ቮልት ስዊችጊር ተከላ በራስ አቅም የቅየራ ሥራ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ የአቅም ማሻሻያ ሥራዎችን በራስ አቅም ማከናወን መጀመሩና በአነስተኛ ወጭ ማከናወን መቻሉ፣ ቀድሞ በዉጪ ኮንትራክተሮች ይከናወን የነበረዉን የስማርት ሜትር ተከላ ሥራ በራስ ኃይል መከናወኑ የበጀት ዓመቱ ጠናካራ ጎኖች መሆናቸዉን ጠቅሰዋል፡፡
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”