የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2016 በጀት ዓመት በዳታ ማይኒንግ ሥራ ለተሰማሩ ድርጅቶች ካቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ25 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን በተቋሙ የገበያና ቢዝነስ ልማት መምሪያ ገለፀ።
በመምሪያው የሽያጭና ደንበኞች አስተዳደር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ምኒልክ ጌታሁን እንደገለፁት የተቋሙን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ ለሀገር ውስጥ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል በዶላር መሸጥ ተጀምሯል።
ቀደም ሲል ለሀገር ውስጥ ደንበኞች ኤሌክትሪክ በብር ሲሸጥ እንደነበር አስታውሰው ከታህሳስ 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በዳታ ማይኒንግ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዘጠኝ ድርጅቶች የኃይል ሽያጭ ክፍያውን በዶላር እየፈፀሙ እንደሚነኙ አቶ ምኒልክ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቶቹ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ መሰማራታቸውንም ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ በዳታ ማይኒንግ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶቹ 882 ነጥብ 48 ሚሊዮን ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማቅረብ 27 ነጥብ 71 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ 796 ነጥብ 28 ሚሊዮን ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ምኒልክ ገለፃ ለድርጅቶቹ የቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል እና የተገኘው ገቢ ከዕቅዱ አንፃር ከ90 በመቶ በላይ ማሳካተረ ተችሏል።
ድርጅቶቹ በጠየቁት የኃይል ፍላጎት መሠረት በቂ ኃይል ማቅረብ ባለመቻሉ በዕቅዱና በአፈፃፀሙ መካከል ክፍተት መስተዋሉንም ነው ሥራ አስኪያጁ የገለፁት።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”