የወራቤ 132 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ የስልጤ ሕዝብን የዘመናት የኃይል አቅርቦት ጥያቄ የመለሰ መሆኑን የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ገለጹ።
ከንቲባው አቶ ያሲን ከሊል እንደገለጹት የስልጤ ሕዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ባለው የመልማት አቅም ልክ ለመልማት አስተማማኝ የመብራት አቅርቦት እንዲኖረው ሲጠይቅ ቆይቷል።
የወራቤ ከተማና አካባቢው እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ ከጀነሬተር እንዲሁም ከ1999 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ከቡታጅራ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ሲያገኝ መቆየቱን ገልጸዋል።
ሆኖም ከከተማው ዕድገትና ከሕዝቡ የመልማት ፍላጎት አንጻር የነበረው የኃይል አቅርቦት በቂ አልነበረም የሚሉት ከንቲባው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይሄን ፍላጎት ከግምት በማስገባት የወራቤ ማከፋፈያ ጣቢያን መገንባቱን ተናግረዋል።
ለማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ከተማ አስተዳደሩ ከወሰን ማስከበር ጀምሮ በባለቤትነት ስሜት አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
እንደ አቶ ያሲን ገለጻ ቀደም ሲል በኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ቦታ ተረክበው ወደ ሥራ ያለመግባትና አካባቢውም በጸጋው ልክ ያለመልማት ችግር ነበር።
ከማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ጋር ተያይዞ ግን የኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጨመሩንና የንግድና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እያደጉ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
ከንቲባው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስልጤ ሕዝብን የዘመናት የኃይል ጥያቄ የመለሰ የማከፋፈያ ጣቢያ በመገንባቱ እና ከቦታው የተነሱ አርሶ አደሮችን በቋሚነት ለማቋቋም ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
የወራቤ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅና ምክትል ከንቲባ አቶ ሻፊ ሙሲ በበኩላቸው አሁን ላይ ከ215 በላይ ባለሀብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የወራቤ ማከፋፈያ ጣቢያ በመገንባቱ እያደገ የመጣውን የኢንቨስትመንት ጥያቄ ለማስተናገድ ሶጃት የተባለ ከ720 ሄክታር በላይ የኢንዱስትሪ መንደር ከልሎ ለ147 ባለሀብቶች መስጠቱንና እነርሱም በግንባታ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 30 የሚሆኑት ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ምርት ለመግባት የኃይል አቅርቦት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሶጃት መንደርን በክልሉ ዋነኛው የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግና ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የማከፋፈያ ጣቢያው መገንባት ድርሻው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
የወራቤ ማከፋፈያ ጣቢያ ኦፕሬተር ወ/ሪት ማህሌት ጌታቸው እንደገለጹት ጣቢያው ስድስት ወጭ መስመሮች ያሉት ሲሆን አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት በሁለት መስመሮች ብቻ ነው።
ቀሪ አራት መስመሮች በአካባቢው በመገንባት ላይ ለሚገኙ ፋብሪካዎችም ሆነ ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ዝግጁ ናቸው ብለዋል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



