ለሀገር ውስጥ ደንበኞች ቅድሚያ እየተሰጠ ነው

ለሀገር ውስጥ ደንበኞች ቅድሚያ እየተሰጠ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2016 በጀት ዓመት ካመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 84 በመቶ የሚሆነውን ለሀገር ውስጥ ደንበኞች እንዳቀረበ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገለጹ::

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጅነር አሸብር ባልቻ እንደገለጹት በበጀት ዓመት ጥቅም ላይ ከዋለው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 84 በመቶ የሚሆነው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ፣ 9 በመቶ ለውጭ ኤክስፖርት እንዲሁም  ቀሪ 7 መቶው ለተቋሙ የውስጥ አገልግሎት ውሏል።

የ2016 በጀት ዓመት የኃይል አጠቃቀም ከ2015 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ዕድገት እንደነበረው ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የሀገር ውስጥ ፍጆታ በ17 በመቶ እንዲሁም የውጭ ኤክስፖርት በ6 በመቶ እድገት እንደነበረው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላትም ተቋሙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ፍላጎቱን ለማስተናገድ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በአፋጣኝ ማጠናቀቅ እና ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን መጀምር እንደሚጠይቅ አስረድተው ለዚህም የግል አልሚዎችን ያሳተፈ ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

እንደ ኢንጅነር አሸብር ገለፃ እያደገ የመጣውን የሀገር ውስጥ ደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል።

ለጎረቤት ሀገራት ኤክስፖርት እየተደረገ ያለውም ከሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚተርፈውን ኃይል እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ኢንዱስትሪዎችንና በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ታሳቢ በማድረግ የደንበኞቹን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top