በተቋሙ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጥናት ላይ ተመስርቶ መፍታት ይገባል – አቶ ሙላት ገዛኸኝ

በተቋሙ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጥናት ላይ ተመስርቶ መፍታት ይገባል – አቶ ሙላት ገዛኸኝ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጥናት ላይ ተመስርቶ መፍታት እንደሚገባ የተቋሙ የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ ገለፀ፡፡

የኢትዮ ፓወር አካዳሚ ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር “በኢትዮ ኬኒያ ከፍተኛ ቮልቴጅ የቀጥታ መስመር ላይ ያሉ የኦፕሬሽን ተግዳሮቶች እና መፍትሄዎች” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሑፍ ዙሪያ አውደ ጥናት ተካሂዷል፡፡

አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንደገለፁት ተቋሙ የአፍሪካ የኃይል ማዕክል የመሆን ራዕይ ሰንቆ ትልልቅ የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በእነዚህ ሥራዎች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ተልዕኮውን ለማሳካት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ጥናቱን ካለው ተጨባጭ ተሞክሮ ጋር በማቀናጀትና ወደ ተግባር በማውረድ በዘርፉ የሚታየውን ቴክኒካዊ ችግር ለመቅረፍና ለውጥ ለማምጣት መስራት አንደሚገባ አቶ ሙላት ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በተቋሙ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ እና አስፈላጊውን ደጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ጥናቱን ያቀረቡት ዶ/ር ተሾመ ሀንቢሳ እንደተናገሩት የኢትዮ -ኬንያ የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በኢትዮጵያ በኩል የቮልቴጅ መዋዠቅ ችግር የማይታይበት ነው፡፡

ይሁንና በኬንያ በኩል ያለው የቮልቴጅ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ሊፈተሸ የሚገባው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንዲህም ሆኖ ከ2000 ሜጋ ዋት በላይ የማስተላለፍ አቅም ያለው የኃይል ማስተላፊያ መስመር ከኬንያ በኩል ሊፈጠር የሚችለውን የኃይል መዋዠቅ ምንም ጉዳት ሳያደርስ መቋቋም እንደሚችል በጥናታቸው ማረጋገጣቸውንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሁለቱ ሀገራት ይህን ታሳቢ ያደረገ ሥራ በማከናወን የኃይል ማስተላለፍ ሥርዓቱ የተረጋጋ እንዲሆን መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በኢትዮ ፓወር አካዳሚ የምርምር እና ስርጸት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢትወደድ ገብረአሊፍ በበኩላቸው ከኃይል ትስስር ልማት ጋር በተቋሙ የተጠኑ ጥናቶችን እና በተለያዩ አካላት የሚጠኑ ጥናቶች በመገምገም ለተቋሙ አሰራር ፣ ምርታማነትን እና የቴክኖሎጂ ግብዓት አጠቃቀምን በሚያሳድግ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በጥናቱ የተገኘውን ቴክኒካዊ ውጤትና ግኝት መሰረት በማድረግ በቀጣይ በሚከናወኑ ተመሳሳይ ሥራዎች ላይ በመተግበር በኃይል ትስስር የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም አብራርተዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ ከጀነሬሽን፣ ከትራንስሚሽን፣ ከኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፎች እንዲሁም ከኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ የተውጣጡ የሥራ መሪዎችና ሙያተኞች የተሳተፉ ሲሆን ለተነሱ የተለያዩ ቴክኒካዊ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top