ለግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኩ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው

ለግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኩ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው

ለቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በተቋሙ የአግሮ ኢንዱስትሪ የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ አባዲ እንዳስታወቁት ለፓርኩ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ የሚያስችል የማከፋፈያ ጣቢያና ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም ከ37 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡

ለፓርኩ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችለው ሥምምነት ከአራት ዓመት በፊት ቢፈረምም በወቅቱ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ ግንባታው መዘግየቱን አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የምርት እና የፍተሻ ሥራቸውን ያጠናቀቁ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎችን ለማጓጓዝ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ዮናስ ገለፃ ከደብረ-ማርቆስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኩ ድረስ 91 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት እየተሰራ ነው፡፡

የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን የመሠረት ሥራ ለማከናወን የሚያስችሉ ዕቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ እየተጓጓዙ መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ የፕሮጀክቱን ግንባታ በትኩረት በመከታተል በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ስለመታቀዱ ገልፀዋል፡፡

በኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ የፕሮጀክት ማኔጅመንት 2 ሥራ አስኪያጅ አቶ ተድላ ሰይፉ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ መገንባት ለቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ እና በዙሪያው ለሚገኙ ከተሞች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

አራት ትራንስፎርመሮችን ለማስቀመጥ የሚያስችሉ የመሠረት ሥራዎች፣ የመቆጣጠሪያ ክፍል ግንባታዎች እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ እና የኦፕሬተር መኖሪያ ቤቶችን የማጠናቀቅ ሥራዎች እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ጣቢያው ሁለት ባለ 63 እና ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር ትራንስፎርመሮች ያሉት ሲሆን የኃይል መዋዠቅ እንዳያጋጥም ለማድረግ የሚያስችል የካፓሲተር ባንክ እንደሚገጠምለትም አብራርተዋል።

እንደ አቶ ተድላ ገለፃ ጣቢያው ሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥምር ገቢ መስመር እንዲሁም አስር ባለ 33 እና አስር ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ሲኖሩት በነባሩ የደብረ ማርቆስ ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይም ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራ ይከናወናል፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታውን የተቋሙ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት መምሪያ በ12 ወራት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሰራ ሲሆን የቻይናው ሲዋን ኩባንያ ለጣቢያው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ከማቅረብ ባሻገር የፍተሻና ሙከራ ሥራዎችን እንዲሁም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን ደግሞ የህንዱ ካልፓታሩ ኩባንያ እንደሚያከናውኑ ተገልጿል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top