በሰሜን ሪጅን ባለፉት ሦስት ወራት 500 የሚሆኑ የታወር አካላት ተሰርቀዋል

በሰሜን ሪጅን ባለፉት ሦስት ወራት 500 የሚሆኑ የታወር አካላት ተሰርቀዋል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሰሜን ሪጅን በሚገኙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በተፈጸመ ስርቆት 500 የሚሆኑ የተለያየ መጠን ያላቸው የታወር ብረቶች መሰረቃቸውን ሪጅኑ አስታወቁ፡፡

በሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመሮች እና ፋይበር ኦፕቲክስ ጥገና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ህንፃ አረጋዊ እንዳስታወቁት በሪጅኑ ሥር ከሚገኙ 11 የማስተላለፊያ መስመሮች ባለፉት ሦስት ወራት በአራቱ ላይ የኢንስፔክሽን ሥራ ተከናውኗል፡፡

የኢንስፔክሽን ሥራ በተከናወነባቸው በአላማጣ – መሆኒ- መቐለ፣ መቐለ – ተከዜ፣ ተከዜ – አክሱም – ሽሬ እና መቐለ – አድዋ – አክሱም ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ስርቆት ተፈጽሞባቸው መገኘቱን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

በመስመሮቹ ላይ በሚገኙ 41 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሶሶዎች ላይ በተፈፀመ ስርቆት 500 የታወር አካላት በዘራፊዎች ተፈትተው መወሰዳቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በሪጅኑ ያለው የስርቆት መጠን ከሌሎች ሪጅኖች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ህንፃ በአሁኑ ጊዜ መጠኑ ከቦታ ቦታ ቢለያይም ስርቆት የማይፈጸምበት መስመርና አካባቢ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡

የኢንስፔክሽን ሥራ ያልተከናወነባቸው ሌሎች መስመሮች ለስርቆት ተጋላጭ እንደሚሆኑም ስጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ህንፃ ገለፃ በሪጅኑ እየተፈፀመ ያለው ስርቆት መደበኛ የጥገናና የኦፕሬሽን ሥራዎችን ከማከናወን ይልቅ ሪጅኑ በአስቸኳይ የጥገና ሥራዎች ላይ እንዲጠመድ እያደረገው ይገኛል፡፡

ስርቆቱ በሪጅኑ ያለውን የመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት እያባባሰው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳን ባለፉት ሦስት ወራት በሪጅኑ የተፈፀመው የስርቆት መጠን ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የጨመረ ቢሆንም በስርቆቱ ምክንያት የተቋረጠ ኃይል አለመኖሩን አቶ ህንፃ አረጋግጠዋል፡፡

ስርቆትን ለመከላከል ሪጅኑ ለህብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ በስርቆት ተጠርጥረውና እጅ ከፈንጅ በሚያዙ ተጠርጣሪዎቹ ላይ አስተማሪ ቅጣት ባለመሰጠቱ ስርቆትን ለመከላከል እየተከናወነ ያለው ሥራ መፍትሔ ሊያመጣ አልቻለም ብለዋል፡፡

በሰሜን ሪጅን 2 ሺ 32 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች እና 1 ሺ 50 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የማስተላለፊያ መስመር ይገኛል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top