በኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀመው ስርቆት ሀገራዊ ትኩረት የሚሻ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽን ዘርፍ የደቡብ አንድ ሪጅን ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች በኃይል መሰረተ ልማቶች ስርቆት ዙሪያ ተቋሙ ከሚመለከታቸው የመስተዳደር አካላት ጋር በቅርበት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በሰጡት ማብራሪያ በኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ ምሰሶ ብረቶች ላይ እየተፈፀሙ የሚገኙ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል አማራጭ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጠቀም የሚያስችል ጥናት ተጠንቷል።
ጥናቱ ከስርቆት ጋር የተያያዙ ችግሮችን እንዴት መፍታት ይገባል ለሚለው ጥያቄ ቴክኒካዊ መፍትሔ ማስቀመጡን አቶ ሞገስ ገልፀዋል።
የመፍትሔ ሀሳቡ የስርቆት ወንጀሎች በተደጋጋሚ በሚፈፀምባቸው መስመሮች በንዝረት አማካይነት ጥቆማ መስጠት የሚችሉ መሳሪያዎችን መግጠምን ጨምሮ በድሮም በመታገዝ ክትትል ማድረግ የሚቻልባቸው አማራጮችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም ነው ያብራሩት።
ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የመስተዳድር አካላትና የፀጥታ መዋቅሩ የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ለማድረግ ውይይቶች መጀመራቸውንና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ሞገስ ገለፃ በመሠረተ ልማቶቹ ላይ እየተፈፀሙ የሚገኙ የስርቆት ወንጀሎችን ከምንጩ ለማድረቅ የህግ ማዕቀፎችን እስከ ማሻሻል የሚያደርሱ ሀሳቦች በጥናቱ ተካተዋል።
አገልግሎቱ በችግሩ ዙሪያ ትኩረት መስጠቱ በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ስርቆት የብሔራዊ የደህንነት አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።
በኃይል ተሸካሚ ምሰሶ አካላት ላይ እየተፈፀመ ያለው ስርቆት ሀገራዊ ትኩረት በማግኘቱ በአጭር ጊዜ ሒደት ለውጥ እንደሚመጣ እምነታቸውን ገልፀዋል።
እንደ ተቋም የኃይል መሠረተ ልማት ደህንነትን የሚከታተል የሥራ ክፍል መቋቋሙን ገልፀው የሥራ ክፍሉ በየሪጅኖቹ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎችን በመከታተል አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የሪጅን መምሪያዎች በመሰረተ ልማቶቹ አቅራቢያ የሚገኙ በመሆናቸው ከሚመለከታቸው የዞንና ወረዳ የመስተዳድርነና የፀጥታ አካላት ጋር እያደረጉት ያለውን ግንኙነት አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን መምሪያ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች የህብረተሰቡን አመለካከት በመቅረፅ በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀሙ የሚገኙ ስርቆቶችን ለማስቀረት እየሰራ ይገኛል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”






