በሪጅኑ የሚገኙ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል የመጫን አቅማቸው ከ70 በመቶ በላይ ደርሷል

በሪጅኑ የሚገኙ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል የመጫን አቅማቸው ከ70 በመቶ በላይ ደርሷል

በደቡብ አንድ ሪጅን የሚገኙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኤሌክትሪክ የመጫን አቅማቸው ከ70 በመቶ በላይ መድረሱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ
አስታወቀ።

በዘርፉ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ከደቡብ አንድ ሪጅን የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጆች ጋር በኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎች እንዲሁም እያጋጠሙ በሚገኙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ በሐዋሳ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በሪጅኑ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽና ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ ያለው አማረ እንደገለፁት በሪጅኑ ከ132 እስከ 400 ኪሎ ቮልት ኃይል የመጫን አቅም ያላቸው 12 የማከፋፈያ ጣቢያዎች ይገኛሉ።

በአስራ ሁለቱ የማከፋፈያ ጣቢያዎች የተለያየ አቅም ያላቸው 23 ትራንስፎርመሮች እንደሚገኙ  የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ ጣቢያዎቹ በአሁኑ ወቅት ኃይል የማቅረብ አቅማቸው ከ70 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

አስራ ሁለቱ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች 1 ሺህ 910 ሜጋ ዋት ኃይል የመጫን አቅም ቢኖራቸውም በአሁኑ ሰዓት 1 ሺህ 710 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የሻኪሶ፣ ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ ቁጥር 1፣ ይርጋዓለም ቁጥር 1 እና ቡኩሉ ጉማ እንዲሁም ያዶት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ በመሆናቸው የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚያስፈልጋቸው አቶ ያለው ተናግረዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በተያዘው በጀት ዓመት በሪጅኑ በሦስት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የ15/33 ኪሎ ቮልት የጂ.አይ.ኤስ ብሬከር ቅየራ ሥራ ይከናወናል።

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጆቹ በበኩላቸው አንዳንድ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅም ማነስ ችግር እየገጠማቸው በመሆኑ የተበላሹ ትራንስፎርመሮች እና ብሬከሮችን በወቅቱ እንዲጠገኑና እንዲቀየሩ ጠይቀዋል።

ለኦፕሬሽን ሥራ አስፈላጊ የሆነው የተሽከርካሪ አቅርቦት፣ የሥራ ላይ መሳሪያዎች አቅርቦት እና የሰው ኃይል እጥረት በሥራቸው ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ እንዲሟላላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ጣቢያዎቹ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ምቹ የሥራ ከባቢ ከመፍጠር ጀምሮ እየተስተዋሉ ለሚገኙ ችግሮች መፍትሔ እንዲሰጥ አሳስበዋል።

በተቋሙ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ በሪጅኑ በሚገኙ የማከፋፈያ ጣቢያዎች የታዩ ችግሮችን ለመፍታት ዘርፉ ጥረት ያደርጋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top