የጥገናና የማስፋፊያ ሥራዎችን በሪጅኑ አቅም የማከናወን ልምምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምስራቅ 2 ሪጅን ገለጸ።
በሪጅኑ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወርቁ ሙሉ እንደገለጹት ምስራቅ 2 ሪጅን አምስት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እንዲሁም 719 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 1 ሺህ 643 ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ያሉት የማስተላለፊያ መስመሮችን ያስተዳድራል።
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በሁሉም ማከፋፈያ ጣቢያዎችና ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የቅድመ መከላከል፣ ድንገተኛና በዕቅድ ላይ የተመሠረቱ የጥገና የፍተሻ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።


የሪጅኑ ሠራተኞች በተቋሙ ከሚተገበሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲላመዱ ተከታታይ ሥልጠናዎችን በመስጠትና እርስ በእርስ እንዲማማሩ በማድረግ አሁን ላይ የማስፋፊያ እና የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በጎዴ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የማስፋፊያና የጂአይኤስ ብሬከሮች ተከላ ሥራ በራስ አቅም በማከናወን በአካባቢው ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካና የነዳጅ ማጣሪያ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ዝግጁ ማድረግ መቻሉ አብራርተዋል፡፡
የሐረር – ፊቅ ማስተላለፊያ መስመር ላይ ሁለት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች በጎርፍ አደጋ ምክንያት ለመውደቅ ተቃርበው እንደነበር የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ በሪጅኑ አቅም በተከናወነ የመልሶ ግንባታ ሥራ ታወሮቹን ከመውደቅ መታደግ መቻሉንም አስገንዝበዋል።
ከመደበኛ የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎች በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ በጅጅጋ እና ጎዴ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የዕቃ ግምጃ ቤት በመገንባት ንብረቶችን የማደራጀት ሥራ መከናወኑን እንዲሁም በቀብሪደሀርና ፊቅ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታዎች በራስ አቅም እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ሪጅኑ የኃይል መሰረተ ልማቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከአሁን ቀደም ሥርቆት የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች በመለየት የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወኑን የተናገሩት አቶ ወርቁ በዚህም ከሐረሪ ክልል፣ ከኦሮሚያ ክልል የባቢሌ ወረዳ እና ከቀብሪ በያህ የፀጥታ አካላት ጋር ውይይቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ በሥርቆት ምክንያት የወደቀ የከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶ አለመኖሩን አብራርተዋል።




