በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ ሁለት ሪጅን የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ታዬ እንዳስታወቁት በሪጅኑ የተለያየ የኪሎ ቮልት መጠን ያላቸው ስምንት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና 1 ሺ 180 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመሮች አሉ።
በሪጅኑ የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግ ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ በአምስት የማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የማዘመን ሥራዎችን ለማከናወን ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።
በዚህም በወላይታ ሶዶ ቁጥር አንድ ማከፋፈያ በ 33 ኪሎ ቮልት መቆጣጠሪያ ወይም ብሬከር እና በሆሳዕና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ዘመናዊ የጂ አይ ኤስ መቆጣጠሪያ ብሬከሮች ቅየራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በወላይታ ሶዶ ቁጥር አንድ የባለ 15 ኪሎ ቮልት እንዲሁም በሀላባና ሳውላ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮችን በዘመናዊ መቆጣጠሪያዎች ለመቀየር እየተሰራ መሆኑንም አቶ ምትኩ ጠቁመዋል።
ከመቆጣጠሪያ ቅየራው በተጨማሪ በብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አማካይነት በነባሮቹ የወላይታ ሶዶ ሁለተኛ እና አርባምንጭ ቁጥር አንድ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የማስፋፊያ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ከማስፋፊያ ሥራው ጎን ለጎን በፕሮጀክቱ አርባ ምንጭ 2ኛን ጨምሮ ሽግዳንና ቲርጋ ላይ የሚገነቡ ሦስት አዳዲስ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ እንዲሁም የ424 ኪሎ ሜትር የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እየተከናወነ ነው።
ይህም በሪጅኑ ያለውን የኃይል ተደራሽነት በዘላቂነት ለማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ሪጅኑ በሚያስተዳድራቸው ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይም የተጠናከረ የፍተሻ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አቶ ምትኩ ገልጸዋል።
በሪጅኑ የተጠናከረ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች እንደሚከናወኑ የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ለዚህም የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት በማዕከል እንዲሁም በሪጅኑ አቅም የተለያዩ አጫጭርና የሥራ ላይ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ አብራርተዋል።
በኃይል መሠረተ ልማቱ ውስጥ የሚተከሉ ዛፎችና የሚገነቡ ቤቶች እንዲሁም የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ስርቆት ለሪጅኑ ፈተና እንደሆኑበትም ጠቅሰዋል።
ችግሩን ለመከላከል የሚመለከታቸው የጸጥታና የመስተዳድር አካላት እንዲሁም ህብረተሰቡ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

