ማዕከሉ በጣቢያው ያሉ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ ኃሳብ ለማቅረብ እየሰራ ነው

ማዕከሉ በጣቢያው ያሉ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ ኃሳብ ለማቅረብ እየሰራ ነው

በጊቤ ሦስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የተቋቋመው የጥናት፣ ምርምርና ሥልጠና ማዕከል በጣቢያው ያሉ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በጣቢያው የኮሙዩኒኬሽን ኢንጅነርና የማዕከሉ አስተባባሪ አቶ ይስሃቅ ወልደየስ እንዳስታወቁት የማመንጫ ጣቢያው የሚያጋጥሙትን ችግሮች በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት ከሦስት ዓመታት በፊት ማዕከሉን አቋቁሟል።

ማዕከሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ጥናትና ምርምሮችን በመስራት የጣቢያውን የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን ለማቀለጠፍ የሚያግዙ ዘመናዊ አሰራሮችን ለመተግበር ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ማዕከሉ ለጣቢያው የኮሙዩኒኬሽን ሥርዓትና የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን  ተናግረዋል።

የወረቀት ሥራዎችን በዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ለመተካት በጣቢያው ኔትወርክ የሚሰራ “ጊቤ ፕላስ” የተሰኘ መተግበሪያ በልጽጎ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ይስሐቅ ገለፃ መተግበሪያው የእያንዳንዱን የማሽን ታሪክ፣ የንብረት አያያዝ፣ የሰው ኃይሉንና የሚጠቀምባቸውን መሣሪያዎች ኮምፒውተራይዝድ በማድረግ በቀላሉ ታሪካቸውን ለማወቅ የሚያስችል ነው።

መተግበሪያው በወረቀት የነበሩ አሰራሮችን በማዘመን ችግሮችን የቀረፈ ቢሆንም አገልግሎቱን ከዚህ የተሻለ ለማድረግ መተግበሪያውን ለማሻሻል ዕቅድ ተይዞ በመስራት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ማዕከሉ በተለይም በጣቢያው የኮሙዩኒኬሽንና የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የአሰራር ሥርዓቶች ላይ የሚያስፈልጉ ሥልጠናዎችን በመለየት እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

የጥናት፣ ምርምርና ሥልጠና ማዕከላት  በማመንጫ ጣቢያዎች ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ በኩል ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት አቶ ይስሃቅ ይኼን ከግምት በማስገባት በተቋሙ መዋቅር ተፈጥሮለት በሰው ኃይልና በግብዓት የሚደራጅበት መንገድ መታሰብ አለበት ብለዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top